አዲሱን አወቃቀር በመቃወም በምሥራቅ ቦረና ከ50 ሺህ በላይ ተማሪዎች ሳይመዘገቡ መቅረታቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጉጂ ዞን ስር የነበረው ጎሮ ዶላ ወረዳ ነዋሪዎች ምሥራቅ ቦረና በሚል እንደ አዲስ ወደ ተዋቀረው ዞን መካተታቸውን በመቃወም ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለመላክ አለመፈለጋቸውን ገለጹ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና የወረዳው ትምህርት ቢሮ ሠራተኞች እንደገለጹት በዚህም ሳቢያ ከጉጂ ዞን ወደ ምሥራቅ ቦረና ከተጠቃለሉ ወረዳዎች አንዱ በሆነው ጎሮ ዶላ ከ50 ሺህ በላይ ተማሪዎች በተቃውሞ እስካሁን ለዓመቱ ትምህርት አልተመዘገቡም።
በጎሮ ዶሎ ወረዳ ብቻ ከ80 በላይ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የሚናገሩት የወረዳው ትምህርት ቢሮ ሠራተኛ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እስካሁን ድረስ አንድም ተማሪ አለመመዝገቡን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ በአጠቃላይ በክልሉ 11 ሚሊዮን ተማሪዎች ለትምህርት መመዝገባቸውን በመግለጽ ነዋሪዎች የሚያቀርቡት ቅሬታን ያስተባብላል።
በኦሮሚያ ክልል ከወራት በፊት ምሥራቅ ቦረና የሚል አዲስ የዞን መዋቀሩን ተከትሎ የተነሳው ውዝግብ እና ተቃውሞ እስካሁን ድረስ መቋጫ አላገኘም።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ከነሐሴ 25 እስከ ጳጉሜ 5/2015 ዓ.ም. ድረስ የተማሪዎች ምዝገባ ሲያካሂድ ቆይቷል።
ክልሉ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያልተመዘገቡ ተማሪዎች እስከ መስከረም 16/2016 ዓ.ም. ድረስ እንዲመዘገቡ በሚል የምዝገባ ጊዜውን ማራዘሙን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በኦሮሚያ ክልል ሙሉ በሙሉ መስከረም 14/2016 ዓ.ም ትምህርት ተጀመሯል።
የጎሮ ዶላ ወረዳ ሀራ ቀሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሳፋዬ ቶንዶራ አራት ልጆቻቸው እስካሁን ድረስ ለትምህርት አለመመዝገባቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እስካሁን ድረስ በጎሮ ዶላ ወረዳ ትምህርት አልተጀመረም” የሚሉት እኚህ ነዋሪ፣ የወረዳው ነዋሪዎች ምሥራቅ ቦረና ተብሎ ዳግም በተዋቀረው ወረዳ ቅሬታ እንዳላቸው እና በዚህም የተነሳ ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ያስረዳሉ።
ነዋሪዎቹም መዋቅሩ ወደ ቀድሞ ቦታው እስኪመለስ ድረስ ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት አንልክም በማለት ተቃውሞ ማሰማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ከሦስት ወራት ወዲህ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ አላገኙም። የመንግሥት አገልግሎት በወረዳው የለም። ቢሮዎች ዝግ ናቸው፤ ጤና አገልግሎት፣ ትምህርትም ቆሟል” ብለዋል።
ሌላኛው ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የወረዳው ነዋሪ ስድስት ልጆቻቸው ተማሪዎች በመሆናቸው በወረዳው ትምህርት አለመጀመሩ ስጋት ውስጥ ከትቷቸዋል።
“የክልሉ መንግሥት ይህንን ጥያቄ ካልመለሰ ልጆቻችን ያለ ትምህርት ይህንን ዓመት ማሳለፋቸው ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እኚሁ ነዋሪ “ልጆች ተመዝግበው መማር ነበረባቸው። መፍትሄ መስጠት ያለበት አካል ችግሩን መፍታት አለበት። እኛ መልሱን እየጠበቅን ነው። እስካሁን ግን ምንም መፍትሄ የለም። ትምህርት መቆሙ ደግሞ ችግር ነው” ይላሉ።
የጎሮ ዶሎ ወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ሠራተኛ የሆነ እና ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ሌላ ግለሰብ በወረዳው በሚገኙ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ለመማር የተመዘገበ ተማሪ የለም ይላል።
“በ81 ትምህርት ቤቶቸ ሲማሩ ከነበሩ 50 ሺህ በላይ ተማሪዎች እስካሁን አንድም ተማሪ አልተመዘገበም። ይህ በጣም ትልቅ ችግር ነው። የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል።”
ግለሰቡ ነዋሪዎች ያቀረቡትን ቅሬታ መኖሩን አረጋግጦ “የመምህራን ደመወዝ ላለፉት ሦስት ወር አልተከፈለም። ቤተሰቦች ጥያቄዎቸቻችን እስኪመለስ ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት አንልክም በማለት አላስመዘገቡም” ብሏል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ጎሮ ዶሎ ወረዳ የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሲሳይ አሰፋ እና የምሥራቅ ቦረና ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኑራ ዱባ ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ላቀረባለቸው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ የጎሮ ዱላ ወረዳ ጉዳይ በተናጠል ሪፖርት እንዳልደረሰው ነገር ግን በአጠቃላይ በተሳካ ሁኔታ በክልሉ የተማሪዎች ምዝገባ መካሄዱን ገልጿል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኤፍሬም አሰፋ እስካሁን 11 ሚሊዮን ተማሪዎች በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች እና በ44 የኦሮሚያ ከተማ አስተዳዳሮች ውስጥ ምዝገባ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን የገለፁት ኃላፊው፣ አንዳንድ ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸው ወረዳዎች ታይተው የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
“እኛ አስካሁን በእጃችን ላይ ያለው መረጃ አሁን እናንተ ከምትሉት መረጃ ጋር ይፋለሳል። ምክንያቱ ደግሞ ቦረና እና ጉጂ ምዝገባ በትክክል ተካሄዷል፣ ጥሩ አፈጻጸም አሳይተዋል ከተባሉት ውስጥ ናቸው።”
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች አዲስ መዋቅር ሲዘረጋ ከቦረና፣ ከጉጂ እና ከባሌ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎች ተቀናጅተው ምሥራቅ ቦረና ዞን በሚል አዲስ ዞን መስርቷል።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎም “ውሳኔው ሕዝብን አስቀድሞ ያላማከረ ነው” በሚል በጉጂ ዞን የተለያዩ ከተሞች የሰው ሕይወት የነጠቀ ተቃውሞ ሲካሄድ ቆይቷል።












