የናይጄሪያ ፕሬዝዳንቱ ለአገሪቱ ጦር የማስፋፊያ ዕቅድ ፈቃድ ሰጡ

ናይጄሪያውያን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ለአገሪቱ ጦር የማስፋፊያ ዕቅድ ፈቃድ ሰጡ።

በቅርብ ጊዜ ውስጥ ባልታየ ሁኔታ የአገሪቱን ጦር አቅም ለማስፋፋት የተያዘው ዕቅድ የደኅንነት ስጋትን ለመቀልበስ ያለመ ነው ተብሏል።

የማስፋፊያ ዕቅዱ 28,000 ተጨማሪ ወታደሮችን መመልመል እና አራት ወታደራዊ ዕዞችን መጨመርን ያካትታል። አራት አዳዲስ ወታደራዊ ዕዞች ሲጨመሩ አጠቃላይ ቁጥሩ 12 ይደርሳል።

የናይጄሪያ መንግሥት በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች የሚፈጠሩ ነውጦችን እንዲያረግብ ጫናው በርትቶበታል።

ታጣቂ ኢስላሚስቶች፣ ተገንጣዮች እንዲሁም ንጹኃንን አግተው ገንዘብ የሚጠይቁ ወንጀለኛ ቡድኖች ለአገሪቱ የደኅንነት ስጋት ሆነዋል።

ባለፈው ሳምንት በሰሜን ምዕራብ ዛምፋራ ግዛት ታጣቂዎች ቢያንስ 20 ነዋሪዎችን ገድለዋል። በሰሜን ምሥራቅ ናይጄሪያ ቦርኖ ግዛት ደግሞ 46 ተማሪዎች ታግተዋል።

ተማሪዎቹ ከታገቱ ከሰዓታት በኋላ የአገሪቱ ወታደሮች አስለቅቀዋቸዋል።

በቅርብ ጊዜያት ከታጣቂ ቡድኖች ጋር በሚደረገው ትግል የአገሪቱ ጦር ውጤታማ እየሆነ ይመስላል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሆኖም ግን ታጣቂ ቡድኖች የረቀቁ መንገዶችን እየተከተሉ ሲሆን፤ በሚያደርሱት ጥቃትም የናይጄሪያውያን የዕለት ከዕለት ሕይወት ፈተና ውስጥ ወድቋል።

የናይጄሪያ መንግሥት እንዳለው አዲስ ወታደራዊ ዕዞች መጨመራቸው ትብብርን እና የደኅንነት መረጃ መጋራትን የሚያጠናክር ሲሆን፤ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም ያስችላል።

አሁን ባለው አሠራር የተለያዩ የጦሩ ክፍሎች የተለያዩ ግዛቶችን መሸፈን ይጠበቅባቸዋል። ይህም ተከታታይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የግብዓት ውስንነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

በማስፋፊያ ዕቅዱ መሠረት በሰሜን ምሥራቅ እና ማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍል ሦስት አዲስ ወታደራዊ ዋና መቀመጫዎች ይቋቋማሉ።

እነዚህ አካባቢዎች በእስላማዊ ታጣቂዎች እና ሽፍታዎች ጥቃት የሚደርስባቸው እንዲሁም በአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች መካከል ግጭት የሚነሳባቸው ናቸው።

በቅርቡ ጥቃቶች ወደ ደቡብ ናይጄሪያም ተስፋፍተዋል። ያለፈው ግንቦት ላይ በደቡብ ምዕራብ ኦዮ ግዛት በትምህርት ቤቶች ላይ በተፈጸመ የተቀናጀ ጥቃት 44 ተማሪዎች እና መምህራን ታግተዋል።

የናይጄሪያ መንግሥት በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ወታደሮችን ለመመልመል አቅዷል። የደኅንነት ጉዳይ ተንታኞች ለቢቢሲ እንደገለጹት ግን በቅርብ ወራት የናይጄሪያ ወታደሮች በመገደላቸው ምክንያት ወጣቶች ጦሩን እንዲቀላቀሉ ማሳመን ቀላል አይሆንም።

ፕሬዝዳንቱ ለጦሩ ማስፋፊያ ዕቅድ ይሁንታ ከመስጠታቸው በፊት ታጣቂ ቡድኖች "እጅ ካልሰጡ በሙሉ ኃይል እርምጃ እንደሚፈጸምባቸው" አስጠንቅቀዋል።

ባለፈው ወር ባደረጉት ንግግር ከ50,000 በላይ አዲስ የፖሊስ ኃይል እንደሚሰማራ ገልጸዋል። የመከላከያ እና ደኅንነት ዓመታዊ በጀት ወደ 5.41 ትሪሊዮን ዶላር (4 ቢሊዮን ዶላር) ከፍ ማለቱንም አስታውቀዋል።

ያለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ የአሜሪካ እና ናይጄሪያ ኃይሎች በጥምረት ጂሃዲስቶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል።

በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ የሚንቀሳቀሰው ላኩራዋ ታጣቂ ቡድን ላይ የገና በዓል ቀን የወሰዱት እርምጃ ተጠቃሽ ነው።

ለወራት በዘለቀ የአሜሪካ እና ናይጄሪያ ጥምር ኦፕሬሽን የኢስላሚክ ስቴት ከፍተኛ መሪ አቡ-ቢላል አል-ሚኑኪ ተገድሏል።

አይኤስ ባለፉት ዓመታት ባሳየው የጥቃት ዒላማ ለውጥ 90% ትኩረቱን ከሰሃራ በታች ወደሚገኘው የአፍሪካ ክፍል ማዞሩን ተንታኞች ይናገራሉ።

የአይኤስ የናይጄሪያ ክንፍ በንቃት ከሚንቀሳቀሱት መካከል ይጠቀሳል።

የአሜሪካ እና ናይጄሪያ ጥምር ኦፕሬሽን በዚህ ወር መባቻ ላይ ተገባድዷል። የኢስላሚስት ታጣቂዎች ጥቃት ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው።