ሐማስ ታጋቾችን ለቆ፣ ትጥቅ በመፍታት መሪዎቹ ከተሰደዱ ጦርነቱ ነገ ይቆማል፡ ኔታኒያሁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ሐማስ በቁጥጥሩ ስር ያሉ ቀሪ እስራኤላውያን ታጋቾችን በመልቀቅ ትጥቅ የሚፈታ ከሆነ በጋዛ ላይ የሚካሄደው ዘመቻ እንደሚቆም ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ዘመቻ ሂደት ላይ ለውጥ እንድታደርግ የምዕራባውያን አገራት መሪዎች ማስጠንቀቂያ ካወጡ በኋላ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር፣ የፈንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ እንድታቆም አሳስበዋል።

መሪዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ "እስራኤል አዲስ የከፈተችውን ዘመቻ ካላቆመች፣ በእርዳታ አቅርቦት ላይ የጣለችውን ዕቀባ ካላነሳች በምላሹ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ" አስጠንቅቀዋል።

ይህ ያስቆጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ለመሪዎቹ በሰጡት ምላሽ "ሐማስ ከመደምሰሱ በፊት እስራኤል እያካሄደችው ያለውን ኅልውናዋን የመከላከል ጦርነት እንድታቆም እና የፍልስጤም አገር እንዲመሠረት መጠየቅ ሐማስ ለፈጸመው የዘር ማጥፋት ሽልማት መስጠት እና ተጨማሪ ጭፍጨፋን መጋብዝ ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም "ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን ከለቀቀ፣ ትጥቁን ከፈታ፣ ጨፍጫፊ መሪዎቹ ወደ ስደት የሚሄዱ ከሆነ እና ጋዛ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ከሆነች ጦርነቱ ነገ ሊቆም ይችላል" በማለት ከዚህ ያነሰ ነገር እስራኤል እንዳማትቀበል አሳውቀዋል።

እስራኤል ራሷን በመከላከል ሙሉ ድል በሐማስ ላይ እስክትቀዳጅ ድረስ ጦርነቱ የሚቀጥል መሆኑን የጠቀሱት ኔታኒያሁ "ይህ ጦርነት ሥልጣኔ ከኋላ ቀርነት ጋር የሚያደርገው ነው" ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም፣ የፈረንሳይ እና የካናዳ መሪዎች በጋራ ያወጡት መግለጫ ከምዕራባውያን በኩል ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ ጠንከር ያለ ሲሆን፣ በጋዛ ውስጥ ያለው ሰብአዊ ቀውስ በእጅጉ አሳስቧቸዋል።

አገራቱ በጠየቁት መሠረት እስራኤል ምላሽ ካልሰጠች ተጨባጭ እርምጃ እንደሚስዱ ከማስጠንቀቅ ውጪ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስዱ ግን የገለጹት ነገር የለም።

እስራኤል እራሷን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል ያላትን መብት ሁልጊዜ እንደሚደግፉ ያመለከቱት ምዕራባውያኑ መሪዎች፤ "ነገር ግን እየተባባሰ ያለው የእስራኤል እርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም" ብለዋል።

ጨምረውም "አስከፊ" ባሉት ሐማስ በእስራኤል ላይ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በፈጸመው ጥቃት የያዛቸውን ታጋቾች እንዲለቅ ጥሪ አቅርበዋል።

ሐማስ ወደ እስራኤል ዘልቆ በመግባት ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ላለፉት ከ20 ወራት በላይ እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደች የቆየችው ወታደራዊ ዘመቻ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ገድሏል።

ከአንድ ወር በፊት በሐማስ እና በእስራኤል መካከል በተደረሰ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥቃቱ ጋብ ብሎ የቆየ ቢሆንም፤ ጥቃቱ መልሶ አገርሽቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ለረሃብ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት እየገለጹ ነው።

ባለፉት ቀናት እስራኤል በግዛቲቱ ላይ እያካሄድች ባለው ተከታታይ የአየር ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጋዛ ነዋሪዎች መገደላቸውን የጤና ባለሥልጣናት እየገለጹ ነው።

ለሳምንታት ተቋርጦ የነበረው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በተወሰነ መጠን እንዲቀጥል እስራኤል ብትፈቅድም አቅርቦቱ "ውቅያኖስ ላይ ጠብታ የመጨመር" ያህል መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።