ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዝውውር ጭምጭምታዎች፡ ማዲሰን ወደ ኒውካስትል?
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2022/23 የውድድር ዓመት ሊጀመር ጥቂት ቀናት ቀርተውት በሊጉ እውቅ ስም ያላቸው እግር ኳሰኞች ወደ ሌሎች ክለቦች ሊዘዋወሩ እንደሚችሉ ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው።
ኒውካስል ዩናይትድ ከሌስተር ሲቲው ጄምስ ማዲሰን ጋር ስሙ ተያይዞ በስፋት እየተነሳ ነው።
እንደ ፉትቦል ኢንሳይደር ከሆነ፤ ኒውካስል ማዲሰንን ለማስፈረም 60 ሚሊዮን ፓዎንድ መክፈል እንዲመጠበቅበት ሌስተር አስታውቋል።
ቀደም ሲል ኒውካስል የ25 ዓመቱን አማካይ ለማስፈረም 40 ሚሊዮን ፓዎንድ አቅርቦ ነበር ተብሏል።
የሌስተሩ የረዥም ጊዜ ግብ ጠባቂ ካስፐር ሽማይክል 11 ዓመታትን ያሳለፍበትን ክለብ ሊለቅ ተቃርቧል። ዴይሊ ሜይል የ35 ዓመቱ ሽማይክል፤ የፈረንሳዩን ኒስ ክለብ በዚህ ሳምንት ይቀላቀላል ብሏል።
ሊቨርፑል ከቮልስ ካዘዋወረው በኋላ ድንቅ ብቃት ላሳየው አጥቂያቸው ዲያጎ ጆታ አዲስ ውል እንዳቀረቡለት ተገልጿል።
ወደ አንፊልድ ከመጣ ወዲህ ድንቅ ብቃት ያሳየው የ25 ዓመቱ ጆታ ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ እንደተደረገለት ቴሌግራፍ ዘግቧል።
ጆታ እአአ 2020 ላይ ነበር በ45 ሚሊዮን ፓዎንድ ሊቨርፑልን የተቀላቀለው።
አርቢ ላይብዚግ የቼልሲ እና የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ቲሞ ቨርነርን ለማስፈረም ጥረት መጀመሩ ተገልጿል። የጣሊያኑ ጁቬንቱስ ቲሞን ከቼልሲ ለመውሰድ ቀድሞ ፍላጎት አሳይቶ ነበር።
ፋይብሪዚዮ ሮማኖ አርቢ ላይብዚግ እና ቼልሲ በቲሞ ቨርነር ጉዳይ መክረዋል ብሏል።
ፉልሃም ፈረንሳያዊውን ተከላካይ ማላንገ ሳር ለማስፈረም ያቀረቡት ጥያቄ በቼልሲ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። እንደ ስታደርድ ዘገባ ከሆነ፤ ፉልሃም በሳር ምትክ የዌስት ሃሙን የ25 ዓመት የመሃል ተከላካይ ኢሳ ዲዮፕን ለማስፈረም ለለንደኑ ክለብ ጥያቄ አቅርበዋል።
ናፖሊ ግብ ጠባቂውን ኬፓ አሪዛባላጋን በውሰት ለመውደስ ለቼልሲ ጥያቄ ማቅረቡን ስካይ ሰፖርት ዘግቧል። ቼልሲ እአአ 2018 ላይ ዛፓላጋን ለግብ ጠባቂ ክብረ ወሰን የሆነ ገንዘብ ከፍሎ ወደ ምዕራብ ለንደን ቢያስመጣውም፤ የ27 ዓመቱ ኬፓ የተጠበቀውን ያክል ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል።
ኬፓን ለናፖሊ በውስት ሊሰጥ ይችላል የተባለው ቼልሲ፤ አሜሪካዊውን ግብ ጠባቂ ጋብርኤል ስሎኒና ከቺጋጎ ፋየር በውሰት ሊወስድ እንደሚችል ፋብሪዚዮ ሮማኖ ዘግቧል።
ባለፉት ዓመታት የአርሰናል ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ የነበረው ጀርመናዊው በርናድ ሌኖ ፉልሃምን ሊቀላቀል ከጫፍ ድርሷል።
አርሰናል ለ30 ዓመቱ ጀርመናዊ ግብ ጠባቂ 8 ሚሊዮን ፓዎንድ ለመቀበል መስማማቱን ጋርዲያን ዘግቧል።
የአርሰናሉ ወጣት የፊት መስመር ተጫዋች ፎላሪን ባሎጉን የፈረንሳዩን ሬሚስ በውስት ሊቀላቀል መሆኑን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል።