የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ሆስፒታል ላይ በፈፀመው ወረራ “የከፋ ጥፋት” መድረሱ ተገለጸ

ሠራተኞች ህሙማንን ይዘው ሲወጡ

የፎቶው ባለመብት, UGC

ታትሟል

የእስራኤል ጦር 'በርካታ' የሽብር ተጠርጣሪዎችን ያዝኩበት ባለው በደቡባዊ ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል ላይ በፈፀመው ወረራ የከፋ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ።

የእስራኤል ጦር በወሰደው እርምጃ የሆስፒታሉ ሠራተኞች እና ህሙማን በተኩስ ውስጥ ሆነው ከሆስፒታሉ ለመውጣት ተገደዋል።

የናስር ሆስፒታል ዳይሬክተር በሆስፒታሉ ውስጥ ያለው ሁኔታ “አስከፊ እና አደገኛ” መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ናሄድ አቡ ቴማም እንደተናገሩት በሆስፒታሉ ውስጥ ከበባ እንደነበር እና ለብዙ ሰዓታት የዘለቁ ከባድ ፍንዳታዎች ነበሩ።

በሆስፒታሉ ውስጥ የነበሩ ህሙማን ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው እዚያው ቀርተው የተባበሩት መንግሥታት እና ቀይ መስቀል እንዲታደጋቸው እየተማጸኑ እንደሚገኙም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ናስር በጋዛ አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ ጥቂት ሆስፒታሎች አንዱ ሲሆን በሐማስ እና በእስራኤል መከላከያ ኃይል መካከል ለቀናት የዘለቀ ከባድ ውጊያ ተካሂዶበታል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል አዛዥ ቃል አቀባይ ሬር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ እንዳሉት በእስራኤል ጦር በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ታጣቂዎች መካከል ታጋቾችን ወደ ጋዛ በመውሰድ በጥቅምቱ ጥቃት የተሳተፈ የሐማስ የአምቡላንስ አሽከርካሪ እንዲሁም የፍልስጤም ነጻ አውጭ ግንባር አባል ይገኙበታል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም ከተያዙ እና ከተማረኩ ታጣቂዎች እና የተለቀቁ ታጋቾች የሰጡት ምስክርነት ታግተው የተወሰዱ እስራኤላውያን ቀደም ብሎ በሆስፒታሉ ውስጥ እንደቆዩ ያመለክታል ብለዋል።

ሆኖም በሆስፒታሉ በተከፈተው ዘመቻ የተሳተፈው የእስራኤል ልዩ ኃይል እስካሁን ስለታገቱት እስራኤላውያን ያገኘው መረጃ እንደሌለ እና ፍለጋው እንደቀጠለ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ይህንን የተናገሩት ወረራ በተፈፀመበት ሆስፒታል የህክምና ሠራተኞች ህሙማንን በቃሬዛ (ስትሬቸር) ይዘው በጭስ እና በአቧራ በተሸፈነ ኮሪደር ለማውጣት ሲጣደፉ የሚያሳዩ በቢቢሲ የተረጋገጡ ምስሎች ከወጡ ከሰዓታት በኋላ ነው።

እስራኤል የሐማስ ታጣቂ ቡድን መሽጎበታል ባለችው በኻን ዩኒስ ከተማ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል ላይ “ትክክለኛ እና ውስን ” ያለችውን ዘመቻ መክፈቷን ገልጻ ነበር።

ሐማስ እስራኤል በከፈተችው ዘመቻ አገኘሁት ያለችውን ስኬት ሐሰት ብሎታል።

በናስር ሆስፒታል የቆመ አምቡላንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እስራኤል ሐሙስ ዕለት የከፈተችው ዘመቻ የተጀመረው የእስራኤል ኃይል በአካባቢው የተጠለሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ከሰጠች በኋላ ነው።

ጦሩ የናስር ሆስፒታል ሠራተኞች እና ህሙማን መውጣት እንደማይጠበቅባቸውና ሕሙማንን ማከማቸው እንዲቀጥሉ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር።

በጋዛ የሐማስ የሚመራው ጤና ሚኒስቴር ቃል አባይ ዶክተር አሽራፍ አል ኳድራ ግን ይህ ሐሰት ነው ብለዋል።

ቃል ቀባዩ የእስራኤል ወታደሮች በፅኑ ህሙማን ክፍል ያሉ ህሙማን ያለ ሕክምና ለማስቀረት የሆስፒታሉን ሠራተኞች እንዲወጡ አስገድዷል ብለዋል።

ከሆስፒታል እንዲወጡ ከተደረጉ ሠራተኞች አንዷ የሆነችው የፋርማሲ ባለሙያ ራዋን አል ሙግራቢ በወቅቱ የነበረው ሁኔታ አስከፊ እንደነበር ገልጻለች።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ቢሮ በሕንጻው ላይ የስናይፐር ጥቃት እንደተፈፀመ የቀረቡ ክሶች መኖራቸውን ገልጾ፣ ይህም የዶክተሮችን ፣የህሙማንን እንዲሁም የተፈናቃዮችን ሕይወት አደጋ ላይ መጣሉን ገልጿል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድንም አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የታዘዙ ሰዎች በአካባቢው ቢቆዩም ኢላማ ከመሆን፣ ለቀው ቢወጡም ለቦንብ ጥቃት በሚያጋልጣቸው አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን ገልጿል።

እስራኤል የሐማስ ታጣቂዎች ወደ ግዛቷ በመግባት ባደረሱት ጥቃት አብዛኞቹ ሰላማዊ ሰዎች የሆኑ 1 ሺህ 200 ሰዎች ከተገደሉ እና 253 ሰዎች ታግተው ከተወሰዱ በኋላ የአጸፋ እርምጃ እየወሰደች ነው።

በሐማስ ሚመራው የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈፀመች ባለችው የማያባራ ጥቃት እስካሁን አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ ከ28 ሺህ 600 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።