ሊቨርፑል ከኤቨርተን እና ዌስተሃም ከቼልሲ . . . የተጠባቂዎቹ ደርቢዎች ግምት

ታትሟል

ዘንድሮ አቋሙ እያሽቆለቆለ የሚገኘው ሊቨርፑል በመርሲሳይድ ደርቢ ኤቨርተንን ያሸንፍ ይሆን?

“ለእነሱ ምክንያት መደርደር ማቆም አለብኝ” የሚለው የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን ነው።

ያለፈውን ሳምንት የቡድኑን ውጤት በትክክል መገመቱንም ያስታውሳል።

ከሊቨርፑል እና ኤቨርተን በተጨማሪ ሱቶን በዚህ ሳምንተም የሊጉን ጨዋታዎች ግምት አስቀምጧል።

የሊጉ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ ይከናወናሉ።

ቅዳሜ

ዌስትሃም ከ ቼልሲ

ቼልሲዎች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ጎል አላስተናገዱም። በእነዚህ ጨዋታዎች ያስቆጠሩትም አንድ ጎል ብቻ ነው።

ዌስተሃሞችም ጎል የማስቆጠር ችግር ስላለባቸው ይህ ጨዋታ ብዙ ጎል አያስተናግድም።

ሞሮኳዊው አገወርድ በተከላካይ መስመሩ ላይ መሰለፉ ልዩነት እየፈጠረ ነው።

ግምት፡ 1 - 1

አርሰናል ከ ብሬንትፎርድ

አርሰናል ባለፈው ሳምንት በኤቨርተን በመሸነፉ እና ብሬንትፎርድ ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ባለመሸነፉ ይህ ጨዋታ ይጠበቃል።

ዘንድሮ ብሬንትፎርድን በሜዳው ያሸነፈው ብቸኛው ቡድን አርሰናል ነው።

ረቡዕ ዕለት በሲምሬትስ ማንችስትር ሲቲን ከማስተናገዳቸው በፊት አርቴታ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይፈልጋል።

በኤቨርተን የተሸነፉበት ዘንድሮው ደካማ ጨዋታቸው ነበር። ከዚህ ውጤት ማገገም ይጠበቅባቸዋል።

ግምት፡ 2 - 1

ክሪስታል ፓላስ ከ ብራይተን

ብራይትን ከሚያስመዘግበው ውጤት በተጨማሪ በነጻነት መጫወታቸውን እወደዋለሁ።

ፓላስ በተቃራኒው ካለፉት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው።

ፓላሶች አጥብቀው ስለሚከላከሉ ከዚህ ጨዋታ አንድ ነጥብ ያገኛሉ ብዬ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 - 1

ፉልሃም ከ ኖቲንግሃም ፎረስት

መስከረም ላይ ሁለቱ ቡድኖች ተገናኝተው ፉልሃም 3 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል።

የስቲቭ ኩፐር ቡድን ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ደረጃውን ቢያሻሽልም ይህንን ጨዋታ ፉልሃም ያሸንፋል ብዬ አስባለሁ።

ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ጎል ያላስቆጠረው አሌክሳንደር ሚትሮቪች በዚህ ጨዋታ ጎል ያስቆጥራል በዬ ጠብቃለሁ።

ግምት፡ 2 – 1

ሌስተር ከ ቶተንሃም

ሌስተር ባለፈው ሳምንት አስቶን ቪላን በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል። ይህ ግን ከወራጅነት ነጻ አያደርጋቸውም።

በሌላ በኩል ደግሞ ቶተንሃም ሦስት ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ወጥ አቋም በማሳየት ላይ ይገኛል።

ስፐርሶች በቅጣት ተከላካዩ ክርስቲያን ሮሜሮን እና በጉዳት ደግሞ ሁጎ ሎሪስን ያጣሉ።

ግምት፡ 1 – 2

ሳውዝሃምፕተን ከ ዎልቭስ

አብዛኛዎቹ የሳውዝሃምፕተን ደጋፊዎች ናታን ጆንስ አስልጣኛኝ ሆነው በመሾማቸው ደስተኞች አይደሉም።

ባለፈው ሳምንት አሰልጣኙ ከሰጡት ቃለ መጠይቅ በኋላ በዚህ ጨዋታ ቢሸነፉ የመባረራቸው የጊዜ ጉዳይ ይሆናል።

ቡድኑ በሜዳው ማግኘት ከሚገባው 30 ነጥብ ማሳካት የቻለው ስድሰቱን ብቻ ነው።

ቡድኑ ውጤት ቢጠብቅም ዎልቭስ መሻሻል በማሳየቱ የሚሳካ አይመስልም።

ግምት፡ 0 – 1

በርንማውዝ ከ ኒውካስል

በርንማውዞች ካለባቸው የውጤት ቀውስ እና የመውረድ ስጋት አንጻር ሦስት ነጥብ ለማሳካት ይጫወታሉ።

ባለፈው ሳምንት ከብራይተን ጋር ጥሩ ለመንቀሳቀስ ሞክረው ነበር።

ከኒውካስል ጋር ጥሩ የሚፎካከሩ ቢሆንም የኤዲ ሃዊ ቡድን የሚያሸንፍ ይመስለኛል።

ጨዋታው ብዙ ጎሎችን ባያስተናግድም ኒውካስል ሦስቱን ነጥቦች ያሳክል።

ግምት፡ 0 – 2

እሑድ

ሊድስ ከማንቸስተር ዩናይትድ

ጊዜያዊው አሰልጣኝ ማይክል ስኩባላ ረቡዕ ዕለት ኦልድትራፎርድ ላይ አንድ ነጥብ ቢያሳኩም ከዚህ ጨዋታ በፊት በቋሚ አሰልጣኝ ሊተኩ ይችላሉ።

በሳምንቱ አጋማሽ ምንም ነጥብ አያሳኩም ቢባልም ጥሩ አጀማመር አድርገው አቻ ለመለያየት በቅተዋል።

ብዙ ያልጠሩ ነገሮች ስላሉ ይህንን ጨዋታ መገመት በጣም አስቸጋሪ ነው።

ቢሆንም ጨዋታውን ሊድስ እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 – 1

ማንቸስተር ሲቲ ከ አስቶን ቪላ

በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ የሲቲን ጨዋታ በቀላሉ እንደምገምት ጠብቄ ነበር። አሁን ግን እንደዚያ አይደለም።

ፔፕ ጋርዲዮላ በአርሰናል ላይ ጫና ለመፍጠር ያላቸውን ዕድል በቶተንሃም ተሸንፈው አላሳኩትም።

ኤርሊንግ ሃላንድ ቡድኑን ይጠቅማል አይጠቅምም በሚለው ጉዳይ ላይ እኔ ጉዳቱ አይታየኝም።

ብዙዎቹ የቡድኑ ተጫዋቾች አቋማቸው ወርዷል።

በዚህ ጨዋታ ቪላን የሚያሸንፉ ሲሆን ሃላንድም ጎል ያስቆጥራል።

ግምት፡ 2 – 0

ሰኞ

ሊቨርፑል አቋም መዋዠቅ የዘንድሮዎቹን ጨዋታዎች ለመገመት ከባድ አድርጓቸዋል።

ኤቨርተንም አርሴናልን ያሸንፍ እንጂ ለመገመት ከባድ ቡድን ነው።

በደርቢ ጨዋታዎች የቡድኖች አቋም ሊሻሻል የሚችል ሲሆን የሊቨርፑል ደጋፊዎችም ይህንን ይጠብቃሉ።

ኤቨርተኖች ከአርሴናል ጋር በነበራቸው አቋም እንደሚቀጥሉ እገምታለሁ።

ከኤቨርተን እና ከሊቨርፑል ያለፈው ጨዋታ አቋም በመነሳት አሰልጣኝ ሺን ዳይሽ እንደሚያሸንፉ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1 – 2