ሩሲያ ኪዬቭ ላይ የድሮን ጥቃት ማድረሷ ተገለጸ

ታትሟል

ሩሲያ ኪዬቭ ላይ ተከታታይ የአየር ጥቃት እንዳደረሰች ተገለጸ።

በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ላይ ከደረሰው ድብደባ መካከል በኢራን ሠራሽ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የታገዘ እንደሚገኝበት ተገልጿል።

ከዒላማው ጋር በመላተም የላቀ ጉዳት የሚያደርሰውን ካማካዚ ድሮን ሩሲያ መጠቀሟን የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽሚጋል ተናግረዋል።

የድሮን ጥቃቱ በሦስት ቀጠናዎች ዋነኛ መሠረተ ልማቶችን እንደጎዳና፣ በመላው አገሪቱ በመቶዎች በሚቆጠሩ መንደሮች የኤሌክትሪክ መቋረጥ እንደተከሰ ገልጸዋል። በጥቃቱ ብዙ ሰዎች እንደሞቱም አክለዋል።

ከሳምንት በፊት መዲናዋ በሩሲያ ሚሳኤል በደረሰባት ድብደባ 19 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

የድሮን ጥቃቱ የደረሰው በኪዬቭ እንዲሁም በዲፕሮ እና ሱሚ ቀጠናዎች ነው።

ሩሲያ “የታቀዱ ዒላማዎችን” መምታቷን አስታውቃለች።

ዒላማ የተደረጉት “የዩክሬን ወታደራዊ መቀመጫዎችና የኃይል ማመንጫ ማዕከሎች” እንደሆኑም ሩሲያ ገልጻለች።

በሱሚ ቀጠና የኃይል ማመንጫ ማዕከል ላይ በደረሰው ጥቃት አራት ሰዎች መሞታቸውን የዩክሬን ምክትል የአገር ውስጥ ሚኒስትር የቫን የኒን ተናግረዋል።

“ሩሲያ የኃይል አቅርቦትን ለማቃወስ ስትል የኃይል ማመንጫዎችን ዒላማ አድርጋለች። ምን ያህል ተስፋ እንደቆረጡ ነው የሚያሳየው” ብለዋል።

ሚኮሎቭ በተባለው የወደብ ከተማ የሱፍ አበባ ዘይት ማመላለሻ የጭነት መኪናዎች በድሮን ጋይተዋል።

የዩክሬን አየር ኃይል ባለሥልጣን እንዳሉት፣ ከትላንት ምሽት ጀምሮ 37 ድሮኖች ወድመዋል።

ዛሬ በኪዮቭ የድሮን ጥቃት ሲፈጸም፣ የአየር መሣሪያ መከላከያዎች ሲተኮሱ ነበር። በዚህ ተኩስ የተነሳም ከተማዋ ስትታወክ አርፍዳለች።

ጥቃቱ ወደ መዲናዋ ማዕከል የቀረበ እንደሆነና በአካባቢው የአደጋ ጊዜ መኪና ድምጽ ይሰማ እንደነበር ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ “ጠላት ከተሞቻችንን ሊያጠቃ ይችላል። ሊሰብረን ግን አይችልም” ብለዋል።

የኪዬብ ከንቲባ ቪታሊ ኪልቺኮ “የድሮን ጥቃቱ ዩክሬናውያን ላይ የተቃጣ የዘር ማጥፋት ነው። ሩሲያ ዩክሬንን ያለ ዩክሬናውያን ትፈልጋለች” ብለዋል።

ከተማዋን ከድሮን ጥቃት ለመከላከል የአየር ጥቃት መከላከያ መሣሪያዎች እስከሚደርሱ እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የጥቃቱ ትክክለኛ ዒላማ ባይታወቅም፣ ከከንቲባው ቢሮ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የሰዎች መኖሪያ እንዲሁም መኖሪያ ያልሆኑም አካባቢዎች ላይም ድብደባ ተፈጽሟል።

የኪዬብ ዋና አውራ ጎዳና አቅራቢያ ፍንዳታ እንደነበረም ተገልጿል።

በቅርቡ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ያደረሰችው ድብደባ የአገሪቱ የኃይል አቅርቦት ማዕከሎች ላይ ያነጣጠረ ነው።