ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤርትራ መንግሥት ዜጎች በእጃቸው ያለ ገንዘብን በአንድ ወር ወደ ባንክ እንዲያስገቡ አዘዘ
የኤርትራ መንግሥት ዜጎቹ በእጃቸው ላይ ያለ ገንዘብን በሙሉ እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ጥብቅ ማሳሰቢያ አወጣ።
የኤርትራ ማዕከላዊ ባንክ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው ጥብቅ ማሳሰቢያ፤ በአገሪቱ ውስጥ በግለሰቦች እና በተቋማት እጅ የሚገኝ የአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ (ናቅፋ) በሙሉ ዛሬ የጀመረው የአውሮፓውያን ሐምሌ ወር መጠናቀቂያ ድረስ ወደ ባንክ እንዲገባ አዝዟል።
የኤርትራ ባንክ ባወጣው መግለጫ እያንዳንዱ ዜጋ እና ተቋም የመጠቀም መብት ያለው የአገሪቱ ብሔራዊ ገንዘብ የሆነውን ናቅፋ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ ለየትኛውም ልውውጥ በገንዘቡ ብቻ መጠቀም ግዴታ እንደሆነ ገልጿል።
ስለዚህም ዜጎች እና ተቋማት ያላቸውን ገንዘብ በሙሉ ወደ ባንክ እንዲያስገቡ ከዚያ ውጪ ግን ግለሰቦች እና ተቋማት ገንዘብን በይዞታቸው ውስጥ ማቆየት ሕገ ወጥ መሆኑን አስጠንቅቋል።
በዚህም መሠረት ሁሉም ያላቸውን ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲያስገቡ በተጨማሪም የባንክ ሂሳብ የሌላቸው ሰዎች ወይም ተቋማት እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ያላቸውን ናቅፋ አዲስ አካውንት በመክፈት እንዲያስቀምጡ መመሪያ ተሰጥቷል።
ነገር ግን ይህንን መመሪያ በማያከብሩ እና ገንዘባቸውን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ባንክ በማያስገቡ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ እንሚወሰድ ማዕከላዊ ባንኩ አስጠንቅቋል።
በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ በማያደርጉት ላይ ይወሰዳል የተባለው ሕጋዊ እርምጃ ምን እንደሚሆን የተገለጸ ነገር የለም።
ይህ አዲስ መመሪያ የኤርትራ መንግሥት በውጭ ምንዛሪ ተመን፣ በገንዘብ ዝውውር እና በፍጆታ እቃዎች ላይ ለአስርታት ሲያካሂድ ከቆየው ጥብቅ ቁጥጥር ጋር የሚዛመድ ነው።
ከአስር ዓመት በፊት የኤርትራ መንግሥት አዲስ የመገበያያ ገንዘብ አሳትሞ ባሰራጨበት ጊዜ በለውጡ ሂደት በሕዝቡ እጅ የነበረውን ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወደ ባንክ እንዲገባ አድርጎ ነበር።
በወቅቱ የኤርትራ መንግሥት የገንዘብ ለውጡን ያደረገው "ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር እና የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማረጋጋት ነው" ሲል ምክንያት ሰጥቶ ነበር።
በገንዘብ ለውጡ ሂደት ወደ ባንክ የገባውን ገንዘብ መቆጣጠር የቻለው መንግሥት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ማንኛውም የኤርትራ ዜጋ በሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ ላይ ጥብቅ ገደብ ለመጣል ችሏል።
በዚህም መሠረት በኤርትራ ውስጥ በሚገኝ ባንክ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ከባንክ ሂሳባቸው በአንድ ወር ውስጥ ማውጣት የሚችሉት አምስት ሺህ ናቅፋ ብቻ እንዲሆን ተገድቧል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ በዜጎች የገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ የተጣለው የመጠን ገደብ በሕዝቡ የንግድ ልውውጦች እና የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን እያጓተተ ነው።
ይህ ከባንኮች በሚወጣው የገንዘብ መጠን ላይ የተጣለው ገደብ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በብዙ ገጽታዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ግዢዎች እና ለሌሎች ወጪዎች ገንዘብ የሚፈልጉ ኤርትራውያን በወጣው ጥብቅ ገደብ ምክንያት ለበርካታ ወራት ገንዘብ ከባንክ በማውጣት ለማጠራቀም ይገደዳሉ።
በተጨማሪም እንደ ሰርግ ላሉ ከፍተኛ ወጪን ለሚጠይቁ አንዳንድ ጉዳዮች ከተቀመጠው ወርሃዊ አምስት ሺህ ብር በላይ ከባንኮች ገንዘብ ለማውጣት ከአካባቢያቸው ባለሥልጣን የፈቃድ ደብዳቤ ማግኘት አለባቸው።
አሁን በአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ የወጣው ዜጎች በእጃቸው የሚገኝ ገንዘብን ወደ ባንከ እንዲያስገቡ የሚያዘው ማስጠንቀቂያ የወጣው ባለፉት ዓመታት በሰዎች እጅ ላይ የተጠራቀመውን ናቅፋ ወደ መንግሥታዊው የገንዘብ መዋቅር ለመመለስ፣ መንግሥት በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እና የገንዘብ ዝውውር ላይ ቁጥጥሩን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ይታመናል።
ኤርትራ በአፍሪካ በመንግሥት በጣም ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት የባንክ ሥርዓት ካሏቸው አገራት አንዷ ናት።
በአገሪቱ ዘመናዊ የገንዘብ ዝውውር እና የባንክ አገልግሎት የሌለ በመሆኑ አብዛኛው የገንዘብ ዝውውር እና ግብይት በጥሬ ገንዘብ ብቻ ነው የሚካሄደው።