ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ መንግሥትን እንደሚከስሱ ሲናገሩ የነበሩት የቦንድ አበዳሪዎች እንዴት ከስምምነት ደረሱ?
ከአንድ ወር በፊት ለኢትዮጵያ ገንዘብ ያበደሩ ባለሀብቶች የአገሪቱን መንግሥት እንደሚከስሱ አስታውቀው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ባለ 1 ቢሊዮን ዶላሩን የአገሪቱን "ዩሮቦንድ" የገዙት ባለሀብቶች ባለፈው ሰኔ ላይ ያደረጉት ንግግር ያለ ስምምነት ተጠናቅቆ ነበር።
ትናንት ሰኞ ሰኔ 22/2018 ዓ.ም. ግን የገንዘብ ሚኒስቴር ከባለሀብቶቹ ጋር የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት መደረሱን አስታውቋል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫ እንደሚያስረዳው፤ የተደረሰው ስምምነት በአብዛኛው ከዚህ ቀደም የቀረቡ የድርድር ነጥቦችን የያዘ ነው። ባለሀብቶቹ አሁን እንዲስማሙ ያደረጋቸው ኢትዮጵያ ያቀረበችላቸው አዲስ ማካካሻ ነው።
መንግሥት ያቀረበው መደራደሪያ ባለሀብቶቹ ወደፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ በሚያደገው ሌላ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ድርሻ የመግዛት መብት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ፋይናንስ ተንታኙ ዶ/ር አብዱልመናን መሐመድ አሁን የቀረበው ማካካሻ ለባለሀብቶቹ "ጥሩ ስምምነት ነው" የሚል እምነት አላቸው። የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሆን "ሌላ አማራጭ እንዳልነበረው" ይከራከራሉ።
እንዴት እዚህ ተደረሰ?
ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነውን ዓለም አቀፍ የብድር ቦንድ ይፋ ያደረገችው በ2007 ዓ.ም. ነበር።
በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ይመራ የነበረው መንግሥት ይህንን ቦንድ ያቀረበው በሚገኘው ገንዘብ እንደ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ያሉ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንዱን ለገዙ አካላት 6.625 በመቶ ዓመታዊ ወለድ ለመክፈል ቃል የገባ ሲሆን፣ ከ10 ዓመት በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ አንድ ቢሊዮን ዶላሩን ለመመለስ ተስማምቷል።
ከታኅሣሥ 2016 ዓ. ም. አንስቶ ግን መንግሥት በዓመት ሁለት ጊዜ መክፈል የነበረትን ወለድ አልፈጸመም። በታኅሣሥ 2017 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ መመለስ የነበረበት ቢሆንም ይህም ሊሆን አልቻለም።
የ33 ሚሊዮን ዶላሩ ወለድ ክፍያ አለመፈጸሙ ኢትዮጵያን ዕዳቸውን መክፈል ካልቻሉ ሦስት የአፍሪካ አገራት ተርታ አሰልፏታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚገልጸው ይህንን ብድር ያልከፈለው አገሪቱ እንደ ቻይና ካሉ አበዳሪ አገራት የዕዳ ሽግሽግ ለማግኘት ከምታደርገው ንግግር መርኅ ጋር ስለሚቃረን ነው።
በዚህ ማዕቀፍ አማካኝነት ለኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ የሚያደርገው የአበዳሪ አገራት ኮሚቴ ካስቀመጣቸው መርሆዎች አንዱ ሁሉም አበዳሪ አካላት የሚቀርብላቸው የተበላለጠ መሆን እንደሌለበት ይገልጻል።
ከአበዳሪዎች ጋር በሚኖረው ግንኙነት "ወጥነት እና እኩልነትን ማረጋገጥ" እንደሚፈልግ የሚገልጸው የፌደራል መንግሥትም፤ የዩሮ ቦንዱን ክፍያ በስምምነቱ መሠረት መፈጸም እፎይታ እንዲሰጡ ከተጠየቁ "ሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ጋር የሚደረገውን ውይይት አደጋ ላይ ይጥለዋል" የሚል ስጋቱን ከዚህ ቀደም ገልጿል።
የፋይናንት ተንታኙ ዶ/ር አብዱልመናን እንደሚያስረዱት አበዳሪ አገራት እና ቦንዱን በገዙ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያ ብድር የሰጡበት ምክንያት በመሠረታዊነት የተለያየ መሆኑ ይህንን መርኅ ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ሆኗል።
አገራት ብድር የሚያቀርቡት ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ሌላ ጥቅምን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር አብዱልመናን፤ የቦንዱ ገዢዎች ግን "ነጋዴዎች" መሆናቸውን ያነሳሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የቦንዱን ገዢዎች የወከለው ኮሚቴ በዚህ ዓመት ታኅሣሥ ላይ ከስምምነት ደርሰው ነበር። ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያ የብድር ሽግሽግ የሚያደርጉት አበዳሪ አገራት ከቦንዱ ገዢዎች ጋር የተደረሰው ስምምነት "የተመጣጣኝነት መርኅን በበቂ እንደማያሟላ" በመግለጽ ውድቅ አድርጎታል።
በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የግል አበዳሪዎቹ በድጋሚ ለድርድር ለመቀመጥ ተገድደዋል።
ባለሀብቶቹ ባለፈው ሰኔ ላይ በተደረገው ድርድር የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን እቅድ ውድቅ አድርገዋል። 45 በመቶ የቦንዱን ገዢዎች የሚወክለው ኮሚቴ የኢትዮጵያ መንግሥት በፍርድ ቤት ለማቆም የዛተውም በዚህ ጊዜ ነው።
ስምምነት የተደረሰባቸው ነጥቦች
ገንዘብ ሚኒስቴር ትናንት ሰኞ ያወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው የኢትዮጵያ እና የግል አበዳሪዎች ኮሚቴው ከግንቦት 28 እስከ እሁድ ሰኔ 28/2018 ዓ.ም. ድረስ ድርድር ሲያደርጉ ነበር። በእነዚህ ቀናት የተደረገው ንግግር "በዋና የፋይናንስ ውሎች" ላይ በመርኅ ደረጃ ከስምምነት መደረሱን አስታውቋል።
በዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት መሠረት 1 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የቦንዱ ዋጋ የ12 በመቶ ቅናሽ ይደረግበታል። ይህም ባለሀብቶቹ በመጨረሻ የሚመለስላቸው 880 ሚሊዮን ዶላር እንዲሆን ያደርጋል።
ይህ የቦንዱ ዋጋም ለባለሀብቶቹ የሚከፈለው እስከ ሐምሌ 2021 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በሚፈጸም የአራት ጊዜ ክፍያ ይሆናል። የመጀመሪያው የ180 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሐምሌ 8 ቀን ይፈጸማል።
በሚቀጥለው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ሁለተኛው የ100 ሚሊዮን ዶላር ይከፈላል። በ2020 እና 2021 ዓ.ም. ሁለት ጊዜ 300 ዶላር ተከፍሎ ይጠናቀቃል።
ኢትዮጵያ ከታኅሣሥ 2016 ዓ.ም. አንስቶ ያልከፈለችውን የ99.37 ሚሊዮን ዶላር የወለድ ክፍያም ወዲያውኑ ትፈጽማለች። ቦንዱ ተከፍሎ እስከሚጠናቀቅበት 2021 ዓ.ም. ድረስም 6.15 በመቶ ወለድ መክፈል ትቀጥላለች።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የየቦንድ ገዢዎቹን የወከለውን ኮሚቴ የሥራ ክፍያ 10 ሚሊዮን ዶላር ጨምሮ በብድር ሽግሽጉ ምክንያት ኮሚቴው ያወጣቸውን ወጪዎች ትሸፍናለች።
የቦንድ ገዢዎችን ያስማማው አዲሱ ማካካሻ
የፋይናንስ ተንታኙ ዶ/ር አብዱልመናን እንደሚገልጹት የቦንዱ ዋጋ ላይ ቅናሽ የተደረገባቸው እና ሙሉ ክፍያው እስከ 2021 ዓ.ም. የተራዘመባቸው ባለሀብቶችን ያስማማው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበው "የገንዘብ ዋስትና" (Money Warrant) የሚል አዲስ ማካካሻ ነው።
ገንዘብ ሚኒስቴርም ባወጣው መግለጫ፤ በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እንዲቻል የግል አበዳሪዎቹ ኮሚቴ ግንቦት ላይ ውድቅ ካደረገው ዕቅድ በተጨማሪ አዲስ አማራጭ መቅረቡን አስታውቋል።
ይህ አዲስ አማራጭ ኢትዮጵያ ወደፊት አዲስ እስከ አንድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ዩሮቦንድ ለሽያጭ በምታቀርብበት ጊዜ እኚሁ ባለሀብቶች ድርሻ እንዲገዙ መብት የሚሰጣቸው አማራጭ ነው። ባለሀብቶቹ በአዲሱ ቦንድ ውስጥ የሚኖራቸው ድርሻ የሚወሰነው በአሁኑ ቦንድ ውስጥ ባላቸው የገንዘብ መጠን ልክ ነው።
እንደ ዶ/ር አብዱልመናን ገለጻ፤ ወደፊት ለገበያ ይቀርባል የተባለውን ቦንድ ለባለሀብቶቹ ተስማሚ ያደረገው የሚከፍለው ዓመታዊ የወለድ መጠን ከአሁኑ የበለጠ መሆኑ ነው።
በስምምነቱ ላይ የቦንዱ የወለድ መጠን አሁን ተቆርጦ አልተቀመጠም። የወለድ መጠኑ የሚታሰበው ቦንዱ ከሁለት ዓመት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2028 ለገበያ በሚቀርብበት ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት ስድስት ዓመት የሚቆይ የግምጃ ቤት ሰነድ የሚከፍለው የወለድ መጠን ላይ በመመሥረት ነው። የአሜሪካ መንግሥት ቦንድ የሚያቀርበው ወለድ ላይ ደግሞ ተጨማሪ 4.6 በመቶ ወለድ ይታከልበታል።
ዶ/ር አብዱልመናን፤ "ለምሳሌ የአሜሪካ ትሬዠሪ ቦንድ አሁን እንደው ቼክ ብናደርግ በአማካይ ከ4 በመቶ ከፍ ያለ ነው። ይህ ማለት ወደፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንድ ሲያወጣ ወደ 9 በመቶ ወለድ ይመጣበታል ማለት ነው" በማለት ያብራራሉ።
ለአሁኑ ቦንድ ላይ የሚከፈለው ዓመታዊ ወለድ 6.15 በመቶ መሆኑን በማንጸሪያነት የሚያነሱት ዶ/ር አብዱልመናን፤ ባለሀብቶቹ በአዲሱ በስምምነት ቃል የተገባላቸው የወለድ መጠን "ከገበያው በጣም ከፍ ያለ" መሆኑን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ መንግሥትን የመውጫ መንገድ በአስቀምጧል። መንግሥት እስከ ሰኔ 2020 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የብድር ቦንድ ማውጣት የማይፈልግ ከሆነ ለባለሀብቶቹ ክፍያ በመፈጸም የሰጠውን አማራጭ ማስቀረት ይችላል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንድ ለገበያ ባለማውጣቱ የሚከፍለው የገንዘብ መጠን የሚወሰነው፤ ለባለሀብቶቹ የሰጠው 'የመግዛት መብት' ወቅታዊ ዋጋ ተተምኖ ነው። ነገር ግን የሚፈጸመው ክፍያ ከ90 ሚሊዮን ዶላር ሊበልጥ እንደማይችል ስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል።
ዶ/ር አብዱልመናን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንዱ ለገበያ ሳያወጣ ይህንን አማራጭ ይከተላል ብለው ያምናሉ። ይህም ቢሆን ግን ባለሀብቶቹ የሚያገኙት የ90 ሚሊዮን ዶላር ጣሪያ "በጣም ብዙ" መሆኑን ይናገራሉ።
በዚህ ስምምነት አማካኝነት ባለሀብቶቹ "ተቻለ መጠን ኪሳራቸውን ለመቀነስ ችለዋል" የሚሉት የፋይናንስ ተንታኙ፤ "በቦንድ ገዢዎቹ አሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባደረጉት ድርድር ያገኙት ስምምነት ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ" ሲሉ ምልከታቸውን አጋርተዋል።
በዚህ ቦንድ ክፍያ ምክንያት ከይፋዊ አበዳሪ አገራት ጋር ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ መድረስ ያልቻው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ይህንን ዓይነቱን መንገድ ከመጠቀም ውጪ "ምንም አማራጭ" እንዳልነበረው ዶ/ር አብዱልመናን ይገልጻሉ። በዚህም ምክንያት "ለኢትዮጵያ መንግሥትም ጥሩ ነው" ብለዋል።
የአሁኑ ስምምነት በአበዳሪ አገራት ተቀባይነት ያገኛል?
የገንዘብ ሚኒስቴር በትናንቱ መግለጫው እንዳስታወቀው፤ ለባለሀብቶቹ የተሰጠው አዲስ የገንዘብ ዋስትን አማራጭ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ቀርቦ ተገምግሟል።
አይኤምኤፍ፤ የስምምነቱ ነጥቦች ለኢትዮጵያ ካስቀመጠው "የዕዳ ዘላቂነት ግቦች እና መለኪያዎች ጋር የሚጣጣም መሆኑን ማረጋገጡ ተገልጿል።
የዕዳ ሽግሽግ የሚያደርገው የአበዳሪ አገራት ኮሚቴ የሚመሩት ፈረንሳይ እና ቻይናም በስምምነቱ ላይ ተቃውሞ እንዳላሰሙ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በቀጣይ ሌሎቹም የኮሚቴው አባላት እንዲያጸድቁት እንደሚቀርብ ጠቅሷል።
ዶ/ር አብዱልመናን፤ የአሁኑ ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ከአበዳሪ አገራት ጋር ያለውን "ጉዳይ ቶሎ እንዲጠናቀቅለት ይረዳዋል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
መንግሥት "አሁን [ከቦንድ ገዢዎቹ] ጋር የጨረሰ እንደሆነ የእዳ ሽግሽግ ጉዳይ በቅርብ ይጠናቀቃል ብዬ እገምታለሁ" ብለዋል።