ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርጀንቲና ውስጥ በአንድ የእግር ኳስ ጨዋታ 10 ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ተባረሩ
አርጀንቲና ውስጥ በተካሄደ አንድ የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ በርካታ ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ በመሰናበታቸው የጨዋታው ሰዓት ከመጠናቀቁ በፊት ግጥሚያው እንዲያበቃ መደረጉ ተዘገበ።
በቦካ ጁኒየርስ እና በሬሲንግ ክለብ መካከል በተካሄደው ግጥሚያ በአጠቃላይ 10 ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ የተባረሩ ቢሆንም ሬሲንግ ክለብ የፍጻሜ ጨዋታው የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።
በርካታ ተጫዋቾች በቀይ ካርድ የተሰናበቱበት ተሸናፊው ቦካ ጁኒየርስ ሲሆን፣ ሁለት ተቀያሪዎችን ጨምሮ ሰባት ተጫዋቾች ከቡድኑ የቀይ ካርድ ሰለባ ሆነዋል።
በጨዋታው ሬሲንግ ክለብ 2 ለ 1 እየመራ ሳለ ነው ቦካ ጁኒየርስ አንድ ቡድን በጨዋታ ወቅት ሊኖሩት ከሚገቡ ተጫዋቾች ያነሰ ቁጥር በቀይ ካርድ ሰበብ በማጣቱ ነው ግጥሚያው እንዲያበቃ የተደረገው።
በእግር ኳስ ደንብ መሠረት በአንድ ጨዋታ ወቅት አንድ ቡድን በሜዳ ውስጥ በቅጣት ምክንያት ከሰባት ተጫዋቾች ያነሱ አባላት ካሉት ግጥሚያው እንዲቋረጥ ይደረጋል።
የሬሲንግ ክለብ ተጫዋች የሆነው ካርሎስ አልካራዝ ግብ አስቆጥሮ ደስታውን በቦካ ጁኒየርስ ደጋፊዎች ፊት በገለጸበት ጊዜ ነበር ውዝግብ ተነስቶ ቀይ ካርድ የተመዘዘው።
በዚህ ወቅት የተቆጡ የቦካ ጁኒየርስ ተጫዋቾች አልካራዝን በመገፈታተር ኳስ ወርውረው መትተውታል።
ይህንንም ተከትሎ ዳኛው ፋኩንዶ ቴሎ፣ አልካራዝንና አምስት የቦካ ጁኒየርስ ተጫዋቾችን ከሜዳ ሲያባርሩ፣ ከሁለቱም ቡድኖች ተቀያሪ ተጫዋቾችም የቀይ ካርድ ሰለባ ሆነዋል።
ጨዋታው ቀጥሎ በቦካው ተጨዋች ሴባስቲያን ቪላ እና በሬሲንጉ ጆን ካርቦኔሮ መካከል ውዝግብ ተነስቶ በቀይ ሲባረሩ፣ ሌላ የቦካ ጁኒየር ቡድን ተጫዋችም በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል።
በአጠቃላይ አስር ተጨዋቾች ቀይ ካርድ ያዩ ሲሆን፣ ከቦካ ጁኒየርስ ቡድን ሰባት ተጫዋቾች፣ ከሬሲንግ ክለብ ደግሞ ሦስት ተጨዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ተባረዋል።
በዚህም ሳቢያ ሁለት ለአንድ እየተመራ የነበረው ቦካ ጁኒየርስ በሜዳው ውስጥ ከሰባት በታች ተጫዋቾች ስለቀሩት፣ የጨዋታው ሰዓት ከማብቃቱ በፊት ግጥሚያው እንዲጠናቀቅ ተደርጎ፣ ሬሲንግ ክለብ አሸናፊ ሆኗል።