በቴክሳስ ልጇን ይዛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተኩስ የከፈተችው ታጣቂ ተገደለች

ጄንሰስ ኢቮኒ ሞሬኖ

የፎቶው ባለመብት, TEXAS DEPARTMENT OF PUBLIC SAFETY

ታትሟል

በአሜሪካ ቴክሳስ በሚገኘው ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከልጇ ጋር የነበረች አንዲት ታጣቂ ለአምልኮ በተሰባሰቡ ምዕመናን ላይ ተኩስ ከከፈተች በኋላ በፖሊስ በተሰጠ አጸፋ ተገድላለች።

ተጠርጣሪዋ ጄንሰስ ኢቮኒ ሞሬኖ እንደምትባል እና ዕድሜዋም 36 እንደነበር ፖሊስ ገልጿል። የኢቮኒ የ7 ዓመት ልጅም በተኩስ ልውውጡ ክፉኛ ተጎድቷል።

መርማሪዎች ታጣቂዋ ይዛው የነበረው መሳሪያ ሰደፍ ላይ “ፍልስጤም” የሚል እና ጸረ ሴማዊ የሆኑ ጽሁፎች እንደተገኙ ተናግረዋል።

ሆኖም ጥቃቱን ለመፈጸም ምክንያት የሆናት ጉዳይ አለመታወቁን አንስተዋል።

ታጣቂዋ በከፈተችው ተኩስ አንድ የ57 ዓመት ግለሰብ ታፋቸው አካባቢ ተመተው የነበረ ሲሆን ከህክምና ክትትል በኋላ ከሆስፒታል ወጥተዋል።

በስም ያልተጠቀሰው የኢቮኒ ልጅ በተኩስ ልውውጡ ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ደርሷል። ታዳጊው ከክስተቱ በኋላ “ለህይወቱ እየታገለ ነው” ነው ተብሏል። ሆኖም ታዳጊው ላይ ማን እንደተኮሰ ግን አልታወቀም።

ይህ ክስተት ሲፈጸም ቤተ ክርስቲያኑ የቀጥታ ስርጭት ላይ የነበረ ሲሆን የተኩስ ድምጽም በሰርጭቱ መካከል ተሰምቷል።

ፖሊስ ጥቃት አድራሿ ሁለት መሳሪያዎችን ታጥቃ እንደነበር እና የተጠቀመችው ግን አንዱን ብቻ እንደሆነ አስታውቋል።

ተኩሱን የከፈተችው ሴት የአእምሮ ጤና ችግር ገጥሟት በአውሮፓውያኑ 2016 በድንገተኛ ማቆያ ውስጥ እንደነበረች ተመላክቷል።

ተጠርጣሪዋ ጥቃት በማድረስ፣ በአደንዛዥ ዕጽ እና ህገ ወጥ መሳሪያ ጋር በተያያዘ ተፈርዶባት ለረዥም ጊዜ እስር ላይ እንደነበረች ተጠቁሟል።

ፖሊስ ጨምሮ በከፊል አይሁድ ከሆኑት የቀድሞ ባለቤቷ ቤተሰቦች ጋር ጸብ ውስጥ ገብታ እንደነበር እንደሚጠረጠር ገልጿል።

ጥቃቱ የደረሰበት ቤተ ክርስቲያን በአሜሪካ ግዙፍ ከሆኑ ቤተ ክርስቲያኖች አንዱ ነው።

በቤተ ክርስቲያኑ የስፓኒሽ ቋንቋ አገልግሎት ሲጀምር ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመዝለቅ ተኩስ መክፈቷ ተነግሯል። ቀጥሎም የቤተ ክርስቲያኑ ጥበቃ የነበሩ ሰዎች በሰጡት የአጸፋ ምላሽ ተገድላለች።

ታጣቂዋ ምንነቱ ያልታወቀ ነገር መሬት ላይ ስትረጭ እንደነበር ፖሊስ ገልጿል። ሆኖም አደጋ የሌለው ነገር እንደሆነ አረጋግጫለሁ ብሏል። ከመሞቷም አስቀድሞ “ቦምብ አለ” እያለች ነበር ያለው ፖሊስ በተደረገ አሰሳ ቦርሳዋም ይሁን መኪና ውስጥ ምንም ፈንጂ አልተገኘም ብሏል።