ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐማስ ከትራምፕ "የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ" በኋላ የአሜሪካ "ሃሳቦች" ላይ መነጋገር ጀመረ
ሐማስ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት መድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በአሸማጋዮች በኩል ከአሜሪካ "አንዳንድ ሃሳቦች"ን መቀበሉን ገለፀ።
የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃሳቦቹን እንዴት ማዳበር እንዳለበት እየተወያየ መሆኑን ገልጾ ጦርነቱን ለማቆም በ"ግልጽ" የሚታወጅ ከሆነ በጋዛ የሚገኙትን 48 ታጋቾችን ለመልቀቅ መዘጋጀቱን ገልጿል።
አንድ የፍልስጤም ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአሜሪካ ዕቅድ የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት በተደረሰ በመጀመርያዎቹ 48 ሰዓታት ውስጥ በሐማስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት ታጋቾቹ አችንዲለቀቁ እና በምትኩ በእስራኤል ወህኒዎች ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እስረኞች እንዲፈቱ የሚል ነው።
ዕቅዱ ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ ይደረሳል የሚል ሃሳብ መያዙም ተገለጿል።
ይህ የተሰማው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሐማስ ከስምምነት ላይ አንዲደርስ "የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ" ከሰጡ በኋላ ነው።
እስራኤል ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ሳትሰጥ የፕሬዚዳንቱን ምክረ ሃሳብ መቀበሏን አስታውቃለች።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር ታጋቾቹን በሙሉ ለማስለቀቅ እና ሐማስን ትጥቅ ማስፈታትን ጨምሮ ጦርነቱን የሚያስቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ አገራቸው ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን በረሃብ በተጠቃችው በጋዛ ከተማ የሚኖሩ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጤማውያን በአስቸኳይ ከተማዋን እንዲለቁ አስጠንቅቀዋል።
የእስራኤል ጦር አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጣር የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሏል።
በቪዲዮ በተላለፈ መልዕክታቸው ላይ "ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ 50 የአሸባሪዎችን ሕንጻዎች አውድመናል፣ እና ይህ በጋዛ ከተማ የምድር ዘመቻ መጀመርያው ነው" ብለዋል።
"ለጋዛ ከተማ ነዋሪዎች የምናገረው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷችኋል፤ ከዚያ ውጡ።"
ሰኞ ዕለት እስራኤል በጋዛ ዙሪያ በፈፀመቻቸው ጥቃቶች ቢያንስ 40 ሰዎችን መገደላቸውን፣ በጋዛ ከተማ እና በሰሜን ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ 25 ሰዎች መሞታቸውን የሆስፒታል ምንጮች ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በሰሜን ጋዛ በተደረገ ውጊያ አራት ወታደሮቹ መገደላቸውን አስታውቋል።
እሁድ ማምሻውን ሐማስ "የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ከአሜሪካ በኩል አንዳንድ ሃሳቦችን በአሸማጋዮች በኩል ተቀብለናል" የሚል መግለጫ አውጥቷል፤ አክሎም ይህ መልካም ጅምር ነው ብሏል።
"ንቅናቄው እነዚህን ሃሳቦች የሕዝባችንን ፍላጎት ወደ ሚያሟላ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ለማዳበር ከአሸማጋዮች ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ያደርጋል" ሲልም አክሏል።
ሐማስ በመስከረም 26 2016 ዓ.ም. ቡድኑ በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት ያገታቸውን እና "ጦርነቱን ለማቆም በይፋ እንዲታወጅ፣ ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ለቀው እንዲወጡ እና ጋዛን የሚያስተዳድር የፍልስጤም ነፃ አውጪዎች ኮሚቴ እንዲቋቋም" በሚል ምትክ ባቆያቸው ታጋቾች ዙሪያ በአስቸኳይ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
ቀደም ሲል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ "ሁሉም ሰው የታገቱትን ወደ ቤታቸው አንዲመለሱ ይፈልጋል፤ ሁሉም ሰው ይህ ጦርነት እንዲያበቃ ይፈልጋል። እስራኤላውያን ሃሳቦቼን ተቀብለዋል ። አሁን ለመቀበል ጊዜው የሐማስ ነው" ብለው ጽፈዋል ።
"ሐማስን አለመቀበል የሚያስከትለውን መዘዝ አስጠንቅቄየዋለሁ። ይህ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያዬ ነው፣ ሌላም አይኖርም!"
የተኩስ አቁም ጥረቱን በቅርበት የሚያውቁ አንድ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአሜሪካ ሀሳብ መሰረት ሁሉም ታጋቾች የ60 ቀን የተኩስ አቁም ስምምነት በተደረሰ በመጀመሪያዎቹ 48 ሰዓታት ውስጥ የሚለቀቁ ሲሆን፤ በምትኩ በእስራኤል እስር ቤት ያሉ ፍልስጤማውያን እስረኞች፣ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው እና ሌሎች የረዥም ጊዜ ፍርደኞች እና ከጋዛ በቁጥጥር ስር የዋሉ ይለቀቃሉ ።
እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ፣ ምክረ ሐሳቡ ጦርነቱን ለማቆም ሁለቱም ወገኖች በቅን ልቦና ድርድር እንደሚያደርጉ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንት የግል ዋስትና መስጠታቸውን አካትቷል።
በተኩስ አቁሙ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ድርድሩ ቁልፍ ጉዳዮችን ማለትም ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት፣ በጋዛ ገለልተኛ የአስተዳደር አካል ወይም የአስተዳደር ኮሚቴ ማቋቋም እና የእስራኤል ወታደሮችን ለቅቀው የመውጣት ዝግጅትን እንደሚያካትት ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ እርዳታም ወደ ጋዛ ያለምንም ገደብ ይገባል።
ማዕቀፉ አፋጣኝ የሰብዓዊ እና የደህንነት ስጋቶችን እየፈታ ሰፊ ሰፈራ ለማካሄድ መንገድ ለመጥረግ ያለመ ይመስላል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የፖለቲካ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው እስራኤል የአሜሪካን እቅድ እያጤነች ቢሆንም ነገር ግን ሐማስ ለመቀበል መቸገሩ አይቀርም ብለዋል።
ሰኞ ዕለት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር በቡዳፔስት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡ "ፕሬዚዳንት ትራምፕ ትናንትና በግልፅ ተናግረው ነበር፣ እስራኤል ያቀረቡትን ሀሳብ እሺ ብላ ተቀብላለች። በካቢኔው ውሳኔ መሠረት ጦርነቱን የሚያቆም ሙሉ ስምምነት ለመቀበል ዝግጁ ነን።
"ሁለት ነገሮች መሆን አለባቸው። አንድ፣ የታጋቾቻችን መመለስ… [ሁለት]፣ ሐማስ ትጥቁን መፍታት አለበት።
የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ በተመሳሳይ ጊዜ ሐማስን "ታጋቾቹን ልቀቁ እና መሳሪያችሁን አስቀምጡ። አለበለዚያ ጋዛ ትወድማለች እና ትጠፋላችሁ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ላይ የአየር እና የምድር ጥቃቶችን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ሰኞ ዕለትም አራተኛው ሕንፃ በደረሰ የአየር ጥቃት ወድሟል።
በቢቢሲ የተመለከተው እና ያረተጋገጠው የቪዲዮ ምስል የአል-ሮያ 2 ሕንፃ በሁለት ሚሳዔሎች ከተመታ በኋላ ወድሟል።