ጆ ባይደን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በጋዛ 'ስህተት' እየሠራ ነው አሉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን
ታትሟል

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ አያያዝ ላይ "ስህተት" እየሠራ ነው ብለው እንደሚያምኑ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።

"እሱ የሚያደርገው ነገር ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ። በእሱ አካሄድ አልስማማም" ሲሉ ባይደን ተናግረዋል።

ጋዛ ለሚቀጥሉት ስድስት እና ስምንት ሳምንታት "ምግብ እና መድሃኒት ማግኘት አለባት" ብለዋል።

አሜሪካ ለጦርነቱ ቀጣይነት ያላት ድጋፍ የሚወሰነው እስራኤል ተጨማሪ ምግብ እና መድኃኒት እንዲገባ በመፍቀዷ ላይ ነው ሲሉ ባለፈው ሳምንት አስጠንቅቀዋል።

እስራኤል ወደ ጋዛ እርዳታ እንዳይገባም ሆነ እንዳይሰራጭ እንቅፋት ሆናለች መባሏን አስተባብላ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት የተፈቀደውን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አላደረሱም ስትል ትከሳለች።

ለሳምንታት የተካሄደው ውይይት የተኩስ አቁም ስምምነትን እንዲደረስ ባያስችልም ዓለም አቀፍ ጫና እየጨመረ መጥቷል።

ባይደን ባለፈው ሳምንት ዎርልድ ሴንትራል ኪችን ሰባት ባልደረቦች በእስራኤል ጦር ጥቃት ከተገደሉ በኋላ በሰቱት ቃለ መጠይቅ የረድኤት ድርጅቱ ተሸከርካሪዎች በሰው አልባ አውሮፕላኖች አውራ ጎዳና ላይ መመታታቸው በጣም አሳፋሪ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት "በከባድ ስህተቶች" ምክንያት ጥቃቱ ደርሷል ብለዋል። በተደረገ ምርመራም ሁለት ከፍተኛ መኮንኖች ከሥራ እንዲባረሩ አድርጓል።

በቃለ መጠይቁ ወቅት ባይደን “እስራኤላውያን የተኩስ ማቆም ጥሪ እንዲያደርጉ፤ ለሚቀጥሉት ስድስት እና ስምንት ሳምንታት ወደ አገሪቱ የሚገቡ ሁሉንም ምግቦች እና መድኃኒቶችን እንዲሰራጩ እጠይቃለሁ” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ቀደም ሲል ሐማስ ተኩስ አቁም አድርጎ የቀሩትን ታጋቾችን ለመልቀቅ መስማማት አለበት ብለዋል።

እስራኤል ወደ ሰሜናዊ ጋዛ መሻገሪያ እና ወደብ በመክፈት ተጨማሪ እርዳታ ወደ አካባቢው እንዲገባ ለማድረግ መወሰኗን አስታውቃለች።

ባይደን በእስራኤል ምክንያት በሀገር ውስጥ ጫና እየገጠማቸው ነው። ለስድስት ወራት በዘለቀው ጦርነት እስራኤል እና ኔታንያሁ ባሳዩት ድርጊት ዙሪያ ላለፉት ሳምንታት የሰላ ትችት ሲሰነዝሩ ታይተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቦምቦች፣ ሚሳኤሎች እና ጥይቶችን ጨምሮ ወታደራዊ ድጋፎች ከአሜሪካ ወደ እስራኤል ያለማቋረጥ መሰጠታቸውን ቀጥለዋል።

የሐማስ ታጣቂዎች መስከረም 26 በደቡባዊ እስራኤል ድንበር በሰነዘሩት ጥቃት አንድ ሺህ 200 ሰዎችን ገድለው ከ250 በላይ አግተዋል።

በጋዛ ከሚገኙት 130 ታጋቾች መካከል ቢያንስ 34ቱ መሞታቸውን እስራኤል ገልጻለች።

ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ጥቃት ከ33 ሺህ በላይ የጋዛ ተወላጆች መሞታቸውን የሐማስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቋል።