በኖርዌይ ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲን ወክሎ ለፓርላማ የተወዳደረው የቀድሞው የኦፌኮ አባል

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ከኢትዮጵያ ወደ ኖርዌይ ከሄደ አስር ዓመት ሆኖታል። ኢትዮጵያ ሳለ በጅማ ዩኒቨርስቲ ለ11 ዓመታት የቋንቋ እና ሥነ ልሳን መምህር ነበር።

የሦስተኛ ዲግሪውን ለመሥራት ነበር ወደ ኖርዌይ ያመራው። በእርግጥ በኢትዮጵያ ሳለ ለፖለቲካ ባዕድ አልነበረም።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አባል በመሆን በፓርቲው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፏል።

ወደ ኖርዌይ ለትምህርት ሲሄድ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ የተቃዋሞ እንቅስቃሴ ተስፋፍቶ ነበር።

የቀድሞው የጅማ ዩኒቨርስቲ መምህር አማኑዔል ራጋ ወደ አገሩ መመለስ ስጋት ሲፈጥርበት በኖርዌይ ኑሮውን አደረገ።

በኖርዌይ ዜግነት አግኝቶ መኖር ከጀመረ ወዲህ ደግሞ ፖለቲካ ውስጥ በመምረጥም ሆነ በመመረጥ መሳተፍ እንዳለበት ወሰነ።

ከዚያም በኋላ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባል ሆኖ መሳተፍ ጀመረ።

ከሁለት ዓመት በፊት ፓርቲውን ወክሎ ለኦስሎ ከተማ ምክር ቤት ተወዳድሮ ነበር።

ያ ተሳትፎ በፈጠረለት ዕድል የኦስሎ አንድ ክፍለ ከተማ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ።

በዚያውም በአካባቢው የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ አስተዳደር አባል መሆን ቻለ።

ኖርዌይ ወደ አገራዊ ምርጫ ስታመራ የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ፓርቲው እንዲሁም ግለሰቦችም ፓርቲውን ወክሎ እንዲወዳደር መረጡት።

አሁን ደግሞ በአገራዊ ምርጫ ላይ ፓርቲውን ወክሎ እየተሳተፈ ነው።

የኖርዌይ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ እጅጉን የተለየ ነው የሚለው አማኑዔል በአገር ቤት የነበረው የፖለቲካ ተሳትፎ ምንም እንዳልረዳው ይናገራል።

"ዲሞክራሲ እና አካታች የሆነ መንፈስ መፍጠርን፣ ተቃዋሚ ቢመጣ እንደ ጠላት ማየት ሳይሆን የራሱ ዕይታ ያለው የአገሪቱ ዜጋ መሆኑን መቀበልን የተማርኩት እዚህ ነው" ሲል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ወቅት ተናግሯል።

በአገሪቱ ውስጥ በርካታ ዕድሎች አሉ የሚለው አማኑዔል "ቁጭ ብሎ ከመመልከት ይልቅ በመሳተፍ የበኩሌን አስተዋጽኦ በማድረግ የምፈልገውን ለመለወጥ ለማምጣት መጣር እንዳለብኝ ወሰንኩ" ይላል።

አማኑዔል በኖርዌይ ፖለቲካ ውስጥ ሰፊ አንቅስቃሴ የሚያደርጉ ፓርቲዎች ቢኖሩም የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲን የመረጠበት ምክንያት በቤተሰብ ዕሴቶች፣ በሰው ልጆች መብት እና በሰብዓዊነት ላይ አተኩሮ ስለሚሠራ መሆኑን ይናገራል።

ቋንቋ እና ባሕሉን ለምዶ በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ

አማኑዔል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የእንግሊዝኛ እና የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ውስጥ ተምሮ በዚያው ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪውን ይዟል።

በ1993 ዓ.ም. በዩኒቨርስቲው ተማሪ በነበረበት ወቅት በወቅቱ አገሪቱን ያስተዳድር የነበረው መንግሥት "በመንግሥት ላይ አምጻችኋል በሚል ለአንድ ዓመት አባረረን" ይላል።

ያኔ ታድያ አማኑዔል ወደ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ በማምራት ኮምፒውተር እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተማረ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በነበረው ቆይታም ለሁለት ዓመት ያህል ጣልያንኛ ተምሯል። በእርግጥ በወቅቱ ቋንቋውን ከቤተብ ጋር በተገናኘ በጣልያንኛ የነበሩ ሰነዶችን አንብቦ ለመረዳት በሚል የተማረው መሆኑን ያስታውሳል።

ስለዚህ ከአማርኛ፣ ከኦሮምኛ እና ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ጣልያንኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ትንሽ ትንሽ አረብኛ ይናገራል።

ኖርዌይ ሄዶም መኖር ሲጀምር "ምንም እንኳን እንደ ልጆች ባይሆንም" ቋንቋውን ለመደበኛ ሥራ ማስኬጃ ያህል መልመድ እንዳልከበደው ይናገራል።

"እንደ ሥነ ልሳን ሰው ከበደኝ ማለት ይከብዳል። በዕድሜ ገፍቶ መጀመር እና ልጅ ሆኖ ቋንቋ መልመድ ልዩነት አለው። ነገር ግን ለሥራ መግባቢያ የሚሆን መልመድ ለማንኛውም ሰው አይከብድም።"

ደግሞም ይላል አማኑዔል የአገሩ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ትንሽ ለየት ስለሚል አያስቸግርም።

ከዚያ በኋላ ቋንቋውን ለሥራ መግባቢያነት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ በጉልህ ለመሳተፍ በሚያስችለው ልክ ለመደ።

በኖርዌይ ውስጥ "የራስህ ዕጣ ፈንታ በራስህ እጅ ነው። በሠራኸው ልክ ነው የምታገኘው" የሚለው አማኑዔል፤ አገሪቱ በመግባባት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ስለምታራምድ በንቃት ለመሳተፍ ተግዳሮት አላጋጠመውም።

በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ለመሳተፍ "ርዕዮተ ዓለም ነው የሚያስፈልገው" በማለት የእርሱ የቆዳ ቀለም፣ ወይንም በስደት ወደ አገሪቱ መግባቱ ተጽዕኖ አለማድረጉን ያስረዳል።

"ለሰው ልጅ እሴት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች የሚገኙት በዚህ ፓርቲ ነው" የሚለው አማኑዔል፤ በፓርቲው ውስጥ በመሳተፍ ለአገሬ ኖርዌይ ማበርከት የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ ይላል።

"ኖርዌይ አሁን ያለችበት ሁኔታ ሁሉ ነገር የተስተካከለ ይመስላል። እርግጥ ከሌሎች አንጻር ጥሩ ደረጃ ላይ ብትገኝም ውስጣዊ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ከወንጀል ከቤተሰብ ጋር ያሉ ነገሮች መስተካከል አለባቸው። ተወዳድሬ የማሸንፍ ከሆነ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚፈቅድልኝ መሠረት እሠራለሁ።"

የተቃውሞ ፖለቲካ በኖርዌይ

የኖርዌይ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ፈጽሞ መለየቱን አማኑዔል አስተውሏል። ከገዢው ፓርቲ የተለየ ሃሳብ ስላለ መሸማቀቅ፣ እታሰራለሁ፣ እሳደዳለሁ ብሎ መስጋት የለም።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል የተለየ ዕይታ እንዳለው አንድ ዜጋ ነው የሚታየው ይላል።

አማኑዔል በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ አብላጫ ድምጽ ያገኙትም ሆነ አነስተኛ ድምጽ ያገኙት እኩል በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ድርሻ እንዳላቸው ይመሰክራል።

የኖርዌይ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ ቀኝ ዘመም (Center right) መሆኑን የሚናገረው አማኑዔል ከዚህ በፊት አብላጫ ድምጽ በማግኘት ለስምንት ዓመታት አገሪቱን ማስተዳደሩን ይናገራል።

ያኔ በተለይ በስደተኞች ላይ መልካም ሥራዎችን እንደሠራ ይነገራል።

ይህ ደግሞ የአማኑዔልን ትኩረት ስቦታል። በክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ ዘር፣ ሃይማኖት ቦታ የላቸውም የሚለው አማኑዔል "ከየት መጣህ ሳይሆን ምን ሃሳብ አለህ" የሚለው ቅድሚያ ያገኛል።

በእርሱ የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥም በመጀመሪያው ምርጫ ብዙ ሰዎች እንዳገዙት ይናገራል።

"በተለይ ስደተኛ ሆነህ ስትመጣ መቼ ተረጋጋቼ ገንዘብ እሠራለሁ? እንጂ ፖለቲካውን ተቀላቅዬ የሚል ሃሳብ ስላልነበር የእኔን በፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጎት ሲያዩ ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ይሆናል በሚል አግዘውኛል።"

በተለይ ለከተማው ምክር ቤት ሲወዳደር እንደ አገሪቱ ልምድ የተለያየ የፖለቲካ ፓርቲ ቢደግፉም እንደ ግለሰብ ግን እርሱን የሚደግፉ በርካታ እንደነበሩ እና ይህም ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገለት ያስረዳል።

በኖርዌይ የትኛውም የፖለቲካ አመለካከት አይጣልም የሚለው አማኑዔል አገሪቱ የምትመራው "መግባባት ላይ በተመሠረተ ፖለቲካ" መሆኗን ይናገራል።

በኖርዌይ ሕገ መንግሥት መሠረት የመራጮችን አብላጫ ማለትም 85 በመቶ ድምጽ ያገኘ አገሪቱን ብቻውን ያስተዳድራል።

ሌሎች ደግሞ ባይመረጡም እንደ የተሳትፏቸው በኮታ የፓርላማ መቀመጫ በማግኘት መንግሥትን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ይሠራሉ።

አለበለዚያ ግን ፓርቲዎች እንዳገኙት ድምጽ ጥምር መንግሥት በመመሥረት ያስተዳድራሉ።

አማኑዔል በዚህ ምርጫ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ቢያሸንፍ በጤና፣ በቤተሰብ፣ በወንጀል መቀነስ ላይ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚፈቅድለት ልክ ለመሥራት አቅዷል።