ሩሲያ የተጠለፈ የጀርመን የጦር መኮንኖች ምሥጢራዊ ስብሰባን የድምጽ ቅጂ ይፋ አደረገች

የጀርመን ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የጀርመን ወታደሮች
ታትሟል

ጀርመን የጦር መኮንኖቿ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን ስለመስጠት እና ጥቃት ስለሚፈጸምባቸው የሩሲያ ዒላማዎች ሲወያዩ የሚሰማበት ስብሰባ የድምጽ ቅጂ በሩሲያ መጠለፉን አመነች።

በቪዲዮ የተካሄደው የወታደራዊ መኮንኖች ስብሰባው የድምጽ ቅጂ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ይፋ የተደረገው በሩሲያ መንግሥት የሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያ አርቲ ሥራ አስኪያጅ ነው።

ሩሲያ ከዩክሬን በኃይል የነጠቀችውን ክራይሚያን ከሩሲያ ጋር የሚያገናኘውን ኬርች የተባለው ድልድይ እንዴት በሚሳኤል ሊመታ እንደሚችል የጀመርመን መኮንኖች ሲወያዩ ይሰማል።

የተጠለፈው ድምጽ ይፋ መሆንን ተከትሎ የሩሲያ ፖለቲከኞች “ደመኛ ጠላት” ያሏቸው ጥቃት እያቀዱ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

የተጠለፈውን ድምጽ በተመለከተ የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ቅዳሜ ዕለት እንደተናገሩት “ክስተቱ ብርቱ ጉዳይ በመሆኑ በጣም በጥንቃቄ፣ በጥልቀት እና በፈጠነ ሁኔታ አሁን ምርመራ እየተደረገበት ነው” ብለዋል።

ዴር ስፒግል የተባለው የጀር መን መጽሔት እንደዘገበው በወታደራዊ መኮንኖቹ መካከል የተደረገው የቪዲዮ ኮንፈረንስ ደኅንነቱ በተጠበቀ የሠራዊቱ የግንኙነት መረብ ሳይሆን ዌብኤክስ በተባለ የበይነ መረብ መድረክ ላይ የተከናወነ ነው።

ባለ 38 ደቂቃው የተጠለፈ የድምጽ ቅጂ ይፋ ያደረገችው የሩሲያ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ኃላፊ ማርጋሪታ ሲሞንያን፣ ጀርመን ክራይሚያ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ዕያቀደች እንደነበር የሚያረጋግጥ ነው ብላለች።

በተጠለፈው የድምጽ ቅጂ ላይ የጦር መኮንኖቹ የዩክሬን ኃይሎች የጀርመን ሥሪት የሆኑትን ታውረስ የተባሉትን ሚሳኤሎች ስለሚጠቀሙበት ሁኔታ እና ስለሚኖረው ተጽእኖ ሲወያዩ ተደምጠዋል።

ታውረስ የተባለው ጀርመን ሠራሽ ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ታውረስ የተባለው ጀርመን ሠራሽ ሚሳኤል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የጀርመን የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የአየር ኃይል መኮንኖች ምሥጢራዊ ውይይት መጠለፉን ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል በማረጋገጥ፣ ነገር ግን ድምጹ ይፋ ከመሆኑ በፊት ማስተካከያ እንደተደረገበት ለማረጋገጥ እንደማይቻል ተናግረዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛኻሮቫ ጀርመን በጉዳዩ ላይ “በአስቸኳይ” ማብራሪያ እንድትሰጥ ጠይቀዋል።

“ጥያቄውን ላለመመለስ የሚደረጉ ሙከራዎች [በድምጽ ቅጂው ላይ] የተባለውን ነገር እንደማመን ይቆጠራል” በማለት ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል።

የሩሲያ የደኅንነት ምክር ቤት ምክትል ኃላፊ እና የፑቲን ቀኝ እጅ የሆኑት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በቴሌግራም ላይ “የዘመናት ተቀናቃኞቻችን - ጀርመኖች - ደመኛ ጠላቶቻችን ሆነዋል” ሲሉ ጠንከር ያሉ ቃላትን ሰንዝረዋል።

“ጀርመኖች በእናት አገራችን እና በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ የሚያስችሉ ዒላማዎችን በጥንቃቄ እና በዝርዝር ግዛታችንን ስለማጥቃት ሲወያዩ እና ሲመርጡ ተመልከቱ” ብለዋል ከፍተኛው ባለሥልጣን።

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ቅዳሜ ዕለት እንደተናገሩት ውይይቱ የጀመርመን ጦር ኃይሎችን “መሰሪ ዕቅድን” ያጋለጠ ዋነኛ ማስረጃ ነው ብለዋል።

ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለምታካሂደው ጦርነት 500 ኪሎ ሜትሮች ያህል በመጓዝ ጥቃት ማድረስ የሚችሉትን ታውረስ የተባሉትን ሚሳኤሎች እንድትሰጣት ትፈልጋለች።

የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ግን ሚሳኤሎቹን መስጠት ግጭቱን ሊያባብሰው ይችላል በሚል ፈቃደኛ ሳይሆኑ አስካሁን ቆይተዋል።

ፈረንሳይ እና ብሪታኒያ ግን 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያሉ ዒላማዎችን መምታት የሚችሉትን ስካልፕ ወይም ስቶርም የተባሉትን ሚሳኤሎችን ለዩክሬን አስታጥቀዋል።

የጀርመን ወግ አጥባቂ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ሮድሪክ ኪስዌተር ተጨማሪ የድምጽ ቅጂዎች ሳይጠለፉ አይቀርም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“በእርግጠኝነት ሌሎች በርካታ ውይይቶች በሩሲያ ተጠልፈዋል፤ በኋላ ላይ ለሩሲያ በሚጠቅም ሁኔታ ይፋ ሊደረጉ ይችላሉ” በማለት ለአንድ የጀርመን መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ጨምረውም የጦር መኮንኖቹ “ውይይት በዚህ ጊዜ በሩሲያ ሆን ተብሎ ይፋ የተደረገው አንዳች ዓይነት ፍላጎትን ለማሳካት” እንደሆነ የገመቱት ፖለቲከኛው፤ ይህም “ጀርመን ታውረስ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን እንዳትሰጥ ለማድረግ ነው” ብለዋል።