ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻይና ባለሥልጣናት ስለወረርሽኙ መረጃዎችን እንዲያጋሩ የዓለም ጤና ድርጅት አሳሰበ
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እየተስፋፋ በመሆኑ የቻይና ባለሥልጣናት ስለወረርሽኙ ወቅታዊ መረጃዎችን ማጋራት አለባቸው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አሳሰበ።
ወረርሽኙን ተከትሎ በርካታ አገራት ጥለውት የነበረውን ገደብ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ አንስተዋል። ነገር ግን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ በርካታ አገራት ከቻይና የሚነሱ መንገደኞችን እየመረመሩ ነው።
በመሆኑም የዓለም ጤና ድርጅት ባለሥልጣናት፣ በቻይና በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል የገቡ፣ ጽኑ ህሙማን ክፍል ያሉ እና ያጋጠመውን የሞት መጠን በተመለከተ ያለውን መረጃ ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ከዚህም ባሻገር የተከተቡ ሰዎችን አሃዝም እንፈልጋለን ብለዋል።
አሜሪካ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሕንድ፣ ጣሊያን፣ ጃፓን እና ታይዋን ቫይረሱ ይዛመታል በሚል ፍራቻ ከቻይና ለሚገቡ መንገደኞች ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ከቻይና ወደ እንግሊዝ የሚገቡ መንገደኞችም አውሮፕላን ውስጥ ከመሳፈራቸው በፊት ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅቱ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር ከተነጋገረ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ በአገሪቷ ስላለው የወረርሽኝ ሁኔታ፣ የክትባት ሥርጭትን እና በተለይም ተጋላጭ የሆኑ እና ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎችን የክትባት ሁኔታ የሚያሳይ ልዩ እና ወቅታዊ የሆነ መረጃን በመደበኛነት እንዲያጋሩ በድጋሚ ጠይቋል።
በዚህ ላይ ድርጅቱ ድጋፍ ለማድረግና ክትባት ለመውሰድ የሚያመነቱ ሰዎችን ጉዳይ ለመፍታት እገዛ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም ቻይና እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትክክለኛ የአደጋ መመዘኛዎችን ለማዘጋጀት እንዲሁም የተገኙ ውጤቶችን ለማሳወቅ ክትትል እና መረጃን በወቅቱ ማጋራት አስፈላጊ መሆኑንም ድርጅቱ አፅንኦት ሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ጤና ድርጅት የቴክኒካል አማካሪ ቡድን በኮቪድ 19 ዝግመተ ለውጥ ላይ ማክሰኞ ስብሰባ ያካሂዳል። በዚህ ስብሰባ ላይም ወረርሽኙን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችን እንዲያቀርቡ የቻይና ተመራማሪዎችን መጋበዙን ድርጅቱ አስታውቋል።
አንዳንድ አገራት ከቻይና በሚነሱ መንገደኞች ላይ ለምን አዲስ ገደብ እየጣሉ እንደሆነም እንረዳለን ብሏል ድርጅቱ።
ቻይና ጥላው የነበረውን ገደብ በድንገት ያነሳችው መንግሥት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሰጠውን ምላሽ አስመልክቶ ኅዳር ወር ላይ ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ ነበር።
እስከዚያ ድረስ ግን ቻይና ዜሮ ኮቪድ ፖሊሲ የተባለ በዓለም ላይ ጥብቅ የሆነ ፀረ ኮቪድ ቁጥጥር ስታደርግ ቆይታ ነበር።
ምንም እንኳን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጥቂት ቢሆኑም፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በተገኙበት ሰፊ ምርመራ እየተካሄደ እና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ራሳቸውን በቤት ውስጥ አሊያም መንግሥት ባዘጋጀው ቦታ እንዲያገሉ ቢደረግም እገዳው ጥብቅ የሆነ የእንቅስቃሴ ገደብን የሚጨምር ነበር።
አሁን ላይ ግን የእቅስቃሴ ገደቡም ሆነ ራስን የማግለል ሕጉ ተነስቷል። በመሆኑም ሰዎች ወደፈለጉት የዓለም ክፍል ለመጓዝ ዳግም ነጻነታቸውን አግኝተዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።
እንደ የቻይና መንግሥት መረጃ ከሆነ በቀን 5 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ። የዘርፉ ተንታኞች ግን መንግሥት የገለጸው ቁጥር ትንሽ መሆኑን ገልጸው በአንድ ቀን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊየን እንደሚጠጋ ተናግረዋል።
የአገሪቷ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በታኅሣሥ ወር ውስጥ በቫይረሱ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 13 ነው።
ተቀማጭነቱን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የጤና መረጃ ድርጅት ኤርፍኒቲ ማክሰኞ ዕለት እንዳመለከተው ግን በቻይና በየቀኑ ወደ 9 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ እየሞቱ ነው።