ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከቻይና በሚነሱ ተጓዦች ላይ አገራት የኮቪድ ምርመራ የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
1.4 ቢሊዮን ሕዝብ ያላት ቻይና 3 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ስትተገብር የነበረውን የኮሮናቫይረስን ስርጭት ዜሮ የማድረስ ፖሊሲ ድንገት ስታቋርጥ በቀጣይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ግልጽ አልነበረም።
ዝቅተኛ የክትባት መጠን እና ተፈጥሮአዊ የበሽታ መከላከል አቅም አለመኖር የኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ያደርጋል።
ቻይና ዜጎቿ ወደ ውጪ አገራት እንዳይበሩ ጥለው የነበረው እገዳ ስታነሳ አንዳንድ የቫይረሱ ስርጭት ዳግም ያገረሻል የሚል ጥርጣሬ የገባቸው።
የተወሰኑ አገራት ከቻይና የሚነሱ መንገደኞች የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርገው ወደ አገራቸው ለመግባት ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥን ግዴታ አድርገዋል።
ቻይና ላይ የተከሰተ አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ባይኖርም ኦሚክሮን የተባለው የቫይረሱዝርያ በተለየ መልክ ተከስቷል።
ይህ በአዲስ መልክ የተከሰተው የቫይረሱ ዝርያ ከዚህ ቀድም ከነበሩት ሁሉ ጠንካራና በፍጥነት የሚተላለፍ ነው።
ሆኖም ይህ የኦሚክሮን ዝርያ ከቻይና ውጪ ባሉ አገራትም ተለይቷል።
በርካታ አገራት ከቻይና የሚነሱ መንግደኞች ላይ ምርመራ ማድረግ ግዴት ያደረጉት ዋነኛ ምክንያት ቻይና በአገሪቱ ኮሮናን የተመለከተ በቂ የክትትል መረጃ ማቅረብ በማቆሟ ነው።
ኮሮና በብዛት እየተሰራጨ በሄደ ቁጥር ቫይረሱ የመቀየር እድሉ ከፍ እያለ እንዲሄድ ያደርገዋል።
ግን አዲሱ ዝርያ የትም አገር ሊከሰት ይችላል። ዩኬ፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሕንድ ቀደም ሲል አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተከሰተባቸው አገራት ናቸው።
ጥያቄው፣ ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ላይ የሚደረገው ምርመራ ለውጥ ያመጣል ወይ ነው?
በርካታ አገራት የቻይና ተጓዦች ወደ አገራቸው እንዲገቡ ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጫ እየጠየቁ ነው።
ተመራማሪዎች አዲስ የኮቪድ ዝርያ የመከሰት እድሉን እየተመለከቱ ባለበት ጊዜ አሜሪካ ይህ አሰራር የቫይረሱ ስርጭት ዝግ እንዲል ያደርጋል ብላለች።
ሆኖም የትኛውም አካል ይህ እርምጃ ኮቪድ-19 እንደ አዲስ ከመቀስቀስ ይገታዋል የሚል ደምዳሜ አልሰጠም።
ጣሊያን ከቻይና የሚነሱ ተጓዦች አገሯ እንደገቡ አስገዳጅ ምርመራ እንዲያደርጉ ይገደደሉ። ቫይረሱ የተገኘባቸው ለበርካታ ቀናት ራሳቸውን እንዲያገሉም ይደረጋል።
ይህም ቫይረሱ ሊያስከትል የሚችለውን አዲስ ዝርያ ለመዋቅ ይረዳል። ግን በአየር ማረፊያዎች ላይ ጫናን ያሰድራል።
የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆረጂያ ሜሎኒ ከቻይና የተነሱ እና እስካሁን ቫይረሱ የተገኘባቸው መንገደኞች ጣሊያን ወስጥ ካለው ዝርያ ጋር የሚመሳሰል የኦሚክሮን ዝርያ እንደተገኘባቸው ተናግረዋል።
ጣሊያን በዚህ ጉዳይ የአውሮፓ ሕብረት እንዲረዳት ብትፈልግም የሕብረቱ የጤና ኤጀንሲ ግን በበርካታ ምክንያት “ልክ ያልሆነ’ ነው ብሏል።
በዩኬም በየሳምንቱ ሚሊዮኖች በኮሮና እንደሚያዙ ይገመታል። ሆኖም ለዜጎች በተሰጠው ተከታታይ ክትባት እና በተደጋጋሚ በተከሰተው ቫይረስ ምክንያት ዜጎቿ የበሽታ መከላክለ አቅምን አዳብረዋል።