ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሦስት ዓመትን ሕጻን ከእንግሊዝ ወደ ኬንያ በመውሰድ ያስገረዘችው ሴት እስር ተፈረደባት
የሦስት ዓመት እንግሊዛዊት ሕጻንን ወደ ኬንያ በመውሰድ ያስገረዘችው ሴት እስር ተፈረደባት።
በሰሜን ምሥራቅ ለንደን፣ ሃሮው ነዋሪ የሆነችው የ40 ዓመቷ አሚና ኑር ሕጻኗን ለማስገረዝ ወደ ኬንያ የወሰደቻት እንደ አውሮፓውያኑ በ2006 ነበር።
ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የወንጀለኞች ፍርድ ቤቱ ኦልድ ቤሊይ ዓርብ ዕለት በዋለው ችሎት ኑር በዚህ ድርጊቷ ሰባት ዓመታትን በእስር እንድታሳልፍ ብይን ሰጥቷል።
ግለሰቧ የዩኬ ዜጋ ያልሆኑ ግለሰብ ግርዛት እንዲፈፅሙ በመተባበር የተፈረደባት የመጀመሪያዋ ግለሰብም ሆናለች።
ኑር ግርዛቱ የተፈፀመው በባህል ምክንያት እንደሆነና እርሷም ሕጻን ሳለች ያለፈችበት እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ብታስረዳም፣ዳኛ ብርያን፣ “ይህ አሰቃቂ እና አስጸያፊ ወንጀል የተጎጂዋን ሕይወት በማይሻር መልኩ ቀይሯል” ሲሉ ውሳኔውን አስተላልፈዋል።
ይህ ወንጀል የተጋለጠው ድርጊቱ ከተፈፀመ ከዓመታት በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 ሲሆን በወቅቱ 16 ዓመት የሆናት ታዳጊዋ ለመምህሯ ከተናገረች በኋላ ነበር።
ከዚያም ወደ ሆስፒታል ሄዳ ምርመራ ተደርጎላታል።
በ2019 በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሆስፒታል የተደረገላት ምርመራም የታዳጊዋ ቂንጥር ( ክሊቶሪስ) ሙሉ በሙሉ መቆረጡን አረጋግጧል።
በችሎቱ ወቅት ዳኛ ብርያን ታዳጊዋ ስለተፈፀመባት ድርጊት ለአስተማሪዋ ለመናገር የነበራትን በራስ መተማመን በማድነቅ ድፍረቷ ሌሎች ሴቶችም የደረሰባቸውን እንዲናገሩ ያነሳሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኑር ተከላከይ ጠበቃ በበኩላቸው በወቅቱ በባህሏ ተቀባይነት ያለውን አስፈላጊውን ነገር እንዳደረገች ነበር ያሰበችው በማለት ባህሏ ተፅዕኖ እንዳሳደረባት በመግለጽ ተከራክረዋል።
አቃቤ ሕግ ዲና ሂር በበኩላቸው የባህል ተፅዕኖውን እንደሚገነዘቡ ገልጸው፣ኑር ታዳጊዋን ከድርጊቱ ለመጠበቅ ጣልቃ አልገባችም ብለዋል።
በሕግ ምክንያት ስሟ ያልተጠቀሰው የ21 ዓመቷ ታዳጊም በፍርድ ቤቱ ባነበበችው መግለጫም ጉዳዩ የሕዝብ መነጋገሪያ መሆኑ ተፅዕኖ እንዳሳደረባት እና ባዕድ ሰዎች ስለ የሰውነት አካሏ ሲወያዩ ምቾት እንዳልተሰማት ገልጻለች።
በችሎቱ ወቅት ኑር ሕጸኗን ወደተገረዘችበት አንድ የግል መኖሪያ ቤት በባጃጅ ከወሰደቻት በኋላ ውጭ እንድትጠብቅ እንደተነገራት ገልጻለች።
ሕጻኗ ባጋጠማት ጉዳትም ስትሰቃይ እንደነበር እና ድርጊቱ ከተፈፀመባት በኋላ ቀን ከሌት ታለቅስ እንደነበር ፍርድ ቤቱ ሰምቷል።
ኑር በፖሊስ በተጠየቀችበት ወቅት ድርጊቱን እንድትፈፅም ማንም ሰው እንዳላስገደዳት ተናግራለች።
ሆኖም ኑር በማኅበረሰቧ የሚደርስባትን 'እርግማን' እና 'መገለልን' በመፍራት የሦስት ዓመቷን ልጅ አሳልፋ እንደሰጠች ተናግራለች።ድርጊቱ ቢያሳምማትም፣ምንም የማድረግ አቅም እንዳልነበራትም ገልጻለች።
በሕጻኗ ላይ ያደረገችው ‘ሱና’ በሚል ወይም በባህል ምክንያት ለረዥም ጊዜ ሲፈፀም የነበረ ድርጊት ነው ብላለች።
ኑር የተወለደችው በሶማሊያ ሲሆን በአገሯ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ነበር የስምንት ዓመት ታዳጊ ሳለች ወደ ኬንያ የሄደችው።
ከዚያም 6 ዓመት ሲሆናት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በማቅናት የእንግሊዝ ዜግነት ማግኘት ችላለች።
በዩኬ የሴት ልጅ ግርዛት መፈፀም አሊያም የእንግሊዝ ዜጋን ወይም ቋሚ ነዋሪዎችን ለማስገረዝ ወደ ሌላ አገር መውሰድ አሊያም ይህንን ከሚያደርግ ሰው ጋር መተባበር ወንጀል ነው።