ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ የሚገኙ 500 ሺህ ገደማ ጥገኝነት ጠያቂ የቬንዙዌላ ዜጎች የመኖሪያ ፍቃድ ተሰጣቸው
የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ይፋ ባደረገው አዲስ ሕግ በአሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ የቬንዙዌላ ዜግነት ያላቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች ሕጋዊ የሥራ ፍቃድ ተሰጣቸው።
ወደ 472 ሺህ የሚጠጉ ቬንዙዌላውያን ለ18 ወራት ለሚቆየው ጊዜ ሕጋዊ ሆነው በአገሪቱ እየኖሩ እንዲሰሩ ተፈቅዶላቸዋል።
ይህ ውሳኔ የተሰማው ዲሞክራቶች ወደ አሜሪካ ለሚገቡ አዳዲስ ስደተኞች የሥራ አማራጮችን ለማስፋት ካደረጉት ጥሪ በኃላ ነው።
የአሜሪካ ከተሞች በርካታ ቁጥር ባላቸውና በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው በተሰደዱ የቬንዙዌላ ዜጎች ተጨናንቀዋል።
ከሐምሌ 24/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወይም ከዚያ በፊት አሜሪካ የገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎች ከአሜሪካ በግዳጅ ከመውጣት እፎይታን የሚያገኙ ሲሆን ጊዜያዊ የስራ ፍቃድም ይሰጣቸዋል።
ፍቃዱን ያገኙ ሰዎች የጥገኝነት ጥያቄያቸውን እየተከታተሉ በአሜሪካ ስራ እንዲሰሩ ተፈቅዶላቸዋል ማለት ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2021 ወጥቶ ባለፈው ዓመት በተራዘመው ሌላ ፖሊሲ 243 ሺህ ቬንዙዌላውያን ጊዜያዊ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል።
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤት ለቬንዙዌላ ዜጎች የተሰጠው ከለላ የተራዘመው ሀገሪቱ ውስጥ እየጨመረ በመጣው አለመረጋጋትና የደህኅንት እጦት ነው ብሏል።
የተራዘመው ከለላ በአሜሪካ የሚገኙ የተመረጡ ሀገራት ዜጎች በግዳጅ ከሀገሪቱ እንዳይወጡ ድጋፍ የሚሰጥ እንደሆነ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ገልጿል።
ሆኖም ከሀምሌ 24/ 2015 ዓ.ም በፊት ወደ አሜሪካ የገቡ ቬንዙዌላውያን ግን በግዳጅ ከአሜረካ እንደሚወጡ እንደሚደረግ ተነግሯል።
የአሜሪካና ሜክሲኮን ድንበር አቋርጠው ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከቅርብ ወራት ወዲህ እየጨመረ መጥቷል። ለዚህም ምክንያቱ የባይደን አስተዳደር ጥብቅ የተባለውን የጥገኝነት ጠያቂዎችን ህግ ውድቅ ማድረጉ ነው።
ይህንን በመቃወም የሪፐብሊካን ተመራጮች ያሉባቸው ግዛቶች ስደተኞች ወደ ዲሞክራቶች ግዛት እያጓጓዙ ነው።
ለዚህም ምክንያት ያሉት በደቡባዊ የአሜሪካ ድንብር በኩል አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ የባይደን አስተዳድር እርምጃ እንዲወስድ ጫና ለመፍጠር ነው።
የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ ግዙፉ የነዳጅ ክምችት ያላትን ቬንዙዌላን ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማድሮ መምራት ከጀመሩበት ከአውሮፐውያኑ 2013 ወዲህ ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሀገራቸውን ጥለው ተሰደዋል።