በምሥራቅ ሐረርጌ የቀድሞ ሚስቱን ችሎት ላይ በጩቤ የገደለው የእድሜ ልክ አስራት ተፈረደበት

የችሎት መዶሻ

የፎቶው ባለመብት, ULLSTEIN BILD

ታትሟል

በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን፣ በደኖ ወረዳ ችሎት ላይ የቀድሞ ባለቤቱን በስለት ወግቶ የገደለው ግለሰብ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።

ግለሰቡ ግድያውን የፈጸመው ባለፈው ዓመት ሰኔ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በበደኖ ወረዳ በተሰየመ ችሎት ላይ ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ በሌላ ሰው ላይም ጉዳት ለማድረስ መሞከሩ ተገልጾ ነበር።

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ዐቃቤ ሕግ አቶ ዘበነ ሺበሺ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ደረጀ ሰይፉ የተባለው ግለሰብ ከቀድሞ ባለቤቱ ትዕግሥት ልክየለው ጋር ከተለያዩ በኋላ በንብረት ክፍፍል ዙሪያ ጉዳያቸው በፍርድ እየታየ ነበር።

ወንጀሉ የተፈጸመው ትዳራቸውን በሕግ አፍርሰው የተለያዩት ጥንዶች በፍርድ ቤት የተያዘው ጉዳይ በሚታይበት ችሎት ላይ ሲሆን፣ ግለሰቡ ቀድሞ የትዳር አጋሩን በስለት ደጋግሞ በመውጋት ነው ለሕልፈት ያበቃት።

የዞኑ ዐቃቤ ሕግ እንዳሉት “በበደኖ ወረዳ ፍርድ ቤት ሳሉ ግለሰቡ ደብቆ ባስገባው ስለት ችሎት ላይ ክርክር እየተካሄደ ሳለ በዳኞች ፊት ነው ደረቷ ላይ በተደጋጋሚ በስለት የወጋት” ብለው፣ ግለሰቧም በተፈጸመባት የስለት ጥቃት ሆስፒታል ከመወሰዷ በፊት ወዲያው ሕይወቷ አልፏል።

ይህ የወንጀል ድርጊት በተፈጸምበት ችሎት አካባቢ የነበረ የፖሊስ አባል ግለሰቡን ሊያስቆም በሞከረበት ጊዜ እሱንም በስለት ሊወጋው ሞክሮ እንደነበረም ተገልጿል።

በቀድሞ ባለቤቱ ግድያ በከባድ የነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሰው ግለሰቡ፣ በተጨማሪም በሕግ አስከባሪ ላይ የግድያ ሙከራ በማድረግ፣ ችሎት በመረበሽ እና የመንግሥት ሥራን ማደናቀፍ በሚሉትን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ክሶች ክሶች ቀርበውበታል።

ተከሳሹ በምሥራቅ ሐረርጌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ የተከሰሰበትን ወንጀል እንዳልፈጸመ ቃሉን በመስጠት ከመከራከሩም በላይ ምስክሮችን በማቅረብ ከቀረቡበት አምስት ክሶች ራሱን ለመከላከል መሞከሩን የዞኑ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።

ነገር ግን ግለሰቡ ያቀረባቸው ምስክሮች ድርጊቱ ሲፈጸም በስፍራው ያልነበ እና ስለወንጀሉ የማያውቁ በመሆናቸው፣ የቀረቡበትን ክሶች በተገቢው ሁኔታ ለመከላከል የሚያስችለው ማስረጃ አላቀረበም ተብሏል።

በዚህም ጉዳዩን ሲመለከት የነበረው ፍርድ ቤት ሰኞ ጥቅምት 5/2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሹን በቀረቡበት ክሶች ሁሉ ጥፋተኛ ነው ሲል በይኖበታል።

የችሎቱ ዳኛ በተከሳሹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ከማስተላለፋቸው በፊት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ እንዳለበት በማመልከት ቅጣት ማክበጃ ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡን ዞን ዐቃቤ ሕግ አቶ ዘበነ ሺበሺ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በመጨረሻ ችሎቱ ተከሳሹ ያቀረበውን የቅጣት ማቅለያን ውድቅ በማድረግ በቀድሞ ሚስቱ ላይ በችሎት ፊት በፈጸመው ከባድ የግድያ ወንጀል ክስ እና በተያያዥ ክሶች የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶበታል።