ግሪክ፡ ሙሽሮች በጫጉላ ቤታቸው እያሉ በጎርፍ ተወሰዱ

ታትሟል

በግሪክ በጫጉላ ሽርሽር ላይ የነበሩ ጥንዶች ያረፉበት ቤት ጎርፍ ይዞት ከሄደ በኋላ መሞታቸው ተረጋገጠ።

አዲሶቹ ሙሽሮች በዜግነት ኦስትሪያዊያን ናቸው።

ጥንዶቹ ከፔልዮን ተራራ አቅራብያ በሚገኝ ሪዞርት ኦፍ ፖሪስቲካ፣ በተባለ ስፍራ አርፈው የነበረ ሲሆን እኤአ መስከረም 6 የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ የሚኖሩበትን ቤት ጠራርጎ ወስዶታል።

የቤቱ ባለቤት አስቀድሞ ከግራዝ የመጡ ናቸው ያለ ሲሆን፣ የኦስተርያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትርም የዲኤንኤ ምርመራ አድርጎ ማንነታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የሚኒስትር መሥርያ ቤቱ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ “በግሪክ የሁለት ኦስትራውያን ሕይወት ማለፉን ሳረጋግጥላችሁ በከባድ ሐዘን ነው። የተደረገው የዲኤን ኤ ምርመራ የጠፉት ሁለት ሰዎች ማንነት አሳውቆናል። ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን” ብሏል።

በአቴንስ የሚገኙ የኦስትርያ ኤምባሲ ባልደረቦች፣ ለጥንዶቹ ቤተሰቦች ድጋፍ ሲሰጡ መቆየታቸውን ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።

ቅዳሜ ዕለት የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱ የገጠማትን ሁኔታ ሲገልጹት “በሰላም ጊዜ ጦርነት ገጥሞናል” ብለው ነበር።

“በሁለት ሳምንት ውስጥ በታሪካችን ከባድ የሆነውን ሰደድ እሳት እና ከባዱን የጎርፍ አደጋ አስተናግደናል” ሲሉም አክለዋል።

ባለፈው ሳምንት ‘ስቶርም ዳንኤል’ የተሰኘው ከባድ ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ ግሪክ፣ ቱርክ እና ቡልጋርያን ካዳረሰ ወዲህ በርካታ ሰዎች የገቡበት ማወቅ አልተቻለም።

የ15 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ይህ ጎርፍ፣ በሺህዎች የሚቆጠሩትን በመጠለያ ጣብያዎች እና ዘመዶቻቸው ጋር እንዲጠለሉ አድርጓል።

30 መንደሮች ደግሞ መንገዶቻቸው በጎርፍ በመወሰዱ ለመድረስ አዳጋች የሆኑ ሲሆን፣ ውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይስፋፋ ተሰግቷል።

መስከረም 8 ለመዝናናት የሚመጡ ሰዎችን ቤት የሚያከራዩ ግለሰብ ለቢቢሲ ሀይለኛ ዝናብ ማዕከላዊ ግሪክን እያጠባት በነበረበት ወቅት፣ ሙሽሮቹ በተከራዩት ጎጆ ውስጥ መቆየት መፈለጋቸውን ተናግረው ነበር።

ሚስተር ሳማራስ እርሱ እና ሌሎች እንግዶች ግን ወደ ኮረብታማ ስፍራ የሄዱ ሲሆን ጥንዶቹም እንዲመጡ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

“ሁኔታው በጣም የከፋ ነበር። በዚያ ቅጽበት ውስጥ ምን ማድረግ እንዳለብህ ለመወሰን አስቸጋሪ ነበር” ብለዋል።

ግሪክ በበጋው ወራት ከሰደድ እሳት ጋር ስትትገል የነበረች ሲሆን ቢያንስ 20 ሰዎችም በዚሁ የተነሳ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በዚህ ከባድ ንፋስ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ የተወሰኑ የግሪክ አካባቢዎች በመደበኛው ወቅት በዓመት ከሚያገኙት የዝናብ መጠን እጅጉን የላቀ ዝናብ አግኝተዋል።

በማዕከላዊ ግሪክ የሚገኘው ካርዲትሳ የሚሰኘው ዝቅተኛ ስፍራ ወደ ባሕርነት መቀየሩን እንዲሁም በፓላማስ የሚገኙ መንደሮች በውሃ መዋጣቸው ተሰምቷል።

የፓላማስ ከንቲባ፣ ለግሪክ ቴሌቪዥን ጣብያ ነዋሪዎች ከቤታቸው መውጣት እንዳልቻሉ በመግለጽ የገጠማቸውን ሁኔታ አሳዛኝ ብለውታል።