አሜሪካ ባለሥልጣናቷን ለመግደል አሲሯል የተባለውን ፓኪስታናዊ ግለሰብ በቁጥጥር ስር አዋለች

አሲፍ መርሻንት በሐምሌ ወር ነው የተያዘው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው ፓኪስታናዊው የአሜሪካ ፖለቲከኞችን እና ባለሥልጣናትን ለመግደል አሲሯል በሚል ክስ ተመሠረተበት።

“በቀጥታ ከኢራን የመነጨ የቅጥረኞች አደገኛ የግድያ ሴራ” ሲሉ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ሬይ ስለ ዕቅዱ ተናግረዋል።

የ46 ዓመቱ አሲፍ ሜርሻንት ታዋቂ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ለመግደል በኒው ዮርክ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ ቀጥሯል በሚል ተከሷል። በአሜሪካ የቢቢሲ የዜና አጋር የሆነው ሲቢኤስ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ ከጥቃቱ ዒላማዎቹ መካከል ይገኙበታል።

የሪፐብሊካኑን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ለመግደል ኢራን ማሴሯ ከተደረሰበት በኋላ የትራምፕ የደህንነት ጥበቃ በሰኔ ወር ተጠናክሯል።

"አንድን ባለሥልጣን ወይም ማንኛውንም የአሜሪካ ዜጋን ለመግደል በውጪ የተጠነሰሰ ሴራ ለብሔራዊ ደህንነታችን ስጋት ነው። በዚህ ላይም ኤፍቢአይ ሙሉ ሃይልና ሃብት ያፈሳል" ሲሉ ሬይ ማክሰኞ ዕለት ተናግረዋል።

ሜርሻንት የታሰረው በሐምሌ ወር ሲሆን አሁን ኒውዮርክ ውስጥ ይገኛል።

የፍትህ ሚኒስቴር ክስ እንደሚያመለክተው ከሆነ መርሻንት በኢራን ቆይታ ካደረገ በኋላ በሚያዝያ ወር ከፓኪስታን ወደ አሜሪካ ገብቷል።

አሜሪካ ከደረሰ በኋላ የግድያውን ሴራ ሊረዳ ይችላል ብሎ ያመነውን ሰው አነጋግሯል ተብሏል። ስሙ ያልተጠቀሰው ግለሰብም በኋላ ላይ ስለመርሻንት ለፖሊስ ሪፖርት አድርጓል።

ሜርሻንት ምን ማድረግ እንደሚፈልግ ተጠይቆ ሲመልስ በእጁ "የጣት ሽጉጥ" እንቅስቃሴ አሳይቷል ተብሏል።

የአሲፍ መርሻንት ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, US Department of Justice

ሜርሻንት ዒላማዎቹ ከመገደላቸው በፊት ከአሜሪካ ለመውጣት እንዳቀደ እና የኮድ ቃላት በመጠቀም ግንኙነቱን እንደሚያስቀጥል ተናግሯል ተብሏል።

ተጠርጣሪው ገዳይ ሊሆኑ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ እንዲያመቻችላቸው ጠይቋል ሲል ክሱ ላይ ሰፍሯል። ግለሰቡም በሰኔ ወር ገዳይ ነው በማለት በድብቅ ከሚንቀሳቀስ የኤፍቢአይ ባልእደረባ ጋር አገናኝቶታል።

ሜርሻንትም ከዒላማ ከተደረገው ባለስልጣን ቤት ሰነዶችን እንዲሰርቁ፣ በፖለቲካ ስብሰባዎች ላይ ተቃውሞ እንዲያዘጋጁ እና "ፖለቲከኛውን" እንዲገድሉ ነግሯቸዋል ተብሏል።

በክሱ መሰረት ሜርሻንት ገዳዮቹ በነሐሴ የመጨረሻ ሳምንት ወይም በመስከረም የመጀመሪያ ሳምንት መረጃ ይደርሳቸዋል ብሏል።

ክሱ ላይ ትራምፕ በስም ባይጠቅሱም፤ የሲቢኤስ የዘገባ ምንጮች ግን የቀድሞው ፕሬዝደንት ከዒላማዎች መካከል አንዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህ ሴራ ፔንስልቬንያ ውስጥ የ 20 ዓመቱ ቶማስ ማቲው ክሩክስ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ ከተካሄደው የግድያ ሙከራ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።

እአአ በ2020 የኢራን ቁድስ ሃይል አዛዥ ቃሲም ሱሌይማኒ በሰው አልባ አውሮፕላን እንዲገደኩ ትዕዛዝ በመስጠታቻው ትራምፕ እና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔን ጨምሮ ሌሎች ባለስልጣናት ከቴህራን ስጋት ተደቅኖባቸዋል።