ጣሊያን በደረሰ የስለት ጥቃት የአርሰናሉ ተጫዋች ፓብሎ ማሪ ጉዳት ደረሰበት

ፓብሎ ማሪ ባለፈው ክረምት ነው ሞንዛን በውሰት የተቀላቀለው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በጣሊያኗ ሚላን ከተማ አቅራቢያ በደረሰ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል በትንሹ አምስት የሚሆኑት ቆስለዋል። አንዳንዶቹ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስተናገዱ ፖሊስ አስታውቋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል በውሰት ጣሊያን በመጫወት ላይ የሚገኘው ፓብሎ ማሪ ይገኝበታል።

አሳጎ በሚባል ስፋራ በደረሰው ጉዳት አንድ የ30 ዓመት የሱፐር ማርኬት ገንዘብ ተቀባይ ሕይወቱ አልፏል።

የ46 ዓመቱ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ውሏል። ፖሊስ ጉዳዩን ከሽብረተኝነት ጋር አይያያዝም ብሏል።

ግለሰቡ የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን ስለቱን ከሱፐርማርኬቱ መደርደሪያ ወስዶ መጠቀሙን ተናግሯል።

ግለሰቡ በከተማዋ በሚገኘው ካርፉር ሱፐርማርኬት ጥቃቱን መፈጸሙ ተነግሯል።

ጥቃቱ ሲፈጸም የደንገጡ ሰዎች ከአካባቢው እየጮኹ ሲሸሹ ታይተዋል።

ብዙ ሰዎች ተጋግዘው ግለሰቡን ለመያዝ የቻሉ ሲሆን ፖሊስ ሲመጣም ማስረከባቸው ታውቋል።

ጀርባው ላይ በስለት የተወጋው ስፔናዊው የ29 ዓመት ተከላካይ ማሪ ለሕይወቱ የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩ ተጠቁሟል። ወኪሉ አርቱሮ ካናሌስ በበኩላቸው ወሳኝ የሰውነት ክፍሉ ላይ ጉዳት አለመድረሱን እና ራሱን እንደሚያውቅ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ማሪ ከባለቤቱ እና ወንድ ልጃቸው ጋር ለግብይት ወጥቶ እንደነበር በውስት የሚጫወትለት የሞንዛ ክልብ ሥራ አስፈጻሚ አድሪያኖ ጋሊያኒ ተናግረዋል።

“ልጁን ተሽከርካሪ እቃ መያዣ ላይ አድርጎ ሚስቱ ደግሞ ከጎኑ ነበረች። ምንም ነገር አላየም ነበር።” ብለዋል ጋሊያኒ።

ጥቃት የተፈጸመበት ሱፐር ማርኬት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

“በሚያሳዝን ሁኔታ ጥቃት አድራሹ የሌላ ሰው አንገት ላይ ጥቃት ሲፈጽም ተመልክቷል። የተፈጸመውን ሁሉ በመመልከቱ በጣም የሚረበሽ ስሜት ነገር ነው” ሲሉ አክለዋል።

ጀርባው ላይ የደረሰበት ጥቃት ጠለቅ ላይ ቁስል ቢፈጥርም ሕይወቱ አደጋ ላይ ካለመሆኑም በላይ  በፍጥነት እንደሚያገግምም ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ማሪ ለአርሰናል የፈረመው ከብራዚሉ ፍላሚንጎ እአአ በ2020 ነበር። 19 ጨዋታዎችን ለመድፈኞቹ ከተጫወተ በኋላ ለጣሊያኑ ሞንዛ ክለብ በውሰት ፈርሟል።

“አሁን መስማቴ ነው። ኤዱ [የአርሴናል ቴክኒካል ዳይሬክተር] ከቤተሰቦቹ ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ አውቃለሁ። ” ሲል የአርሴናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ተናግሯል።