ተመድ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አሜሪካ መቃወሟን ቻይና አወገዘች

የፎቶው ባለመብት, EPA
በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ አሜሪካ መቃወሟን ቻይና በፅኑ አወገዘች።
ቤጂንግ ውሳኔው “የተሳሳተ መልዕክት የሚያስተላልፍ” ሲሆን በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጭፍጨፋ እንዲቀጥል ፈቃድ የሚሰጥ ነው ብላለች።
ዋይት ሃውስ በበኩሉ በአልጀሪያ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገውን ንግግር ያደናቅፋል ብሏል።
አሜሪካ እስራኤል ራፋህ ከተማን እንዳትወር የሚያስጠነቅቅ 'ጊዜያዊ የተኩስ አቁም' እንዲደረግ በግሏ ሃሳብ ያቀረበች ቢሆንም በጋዛ ጦርነት በቀጠለበት ወቅት አልጀሪያ ያቀረበችውን ሃሳብ መቃወሟ ሰፊ ተቃውሞ ገጥሞታል።
በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ከ15ቱ የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት በ13ቱ የተደገፈ ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም ድምጿን አቅባለች።
የውሳኔ ሃሳቡ ለመጽደቅ ቢያንስ የዘጠኝ አባል አገራት የድጋፍ ድምጽ እንዲሁም አሜሪካን ጨምሮ የሁሉም ቋሚ የምክር ቤቱ አባላት ድጋፍ ያስፈልጋል።
የቻይና የተመድ አምባሳደር ዣንግ ጁን የአሜሪካን ውሳኔ ተከትሎ በሰጡት ምላሽ፣ ውሳኔው እየተካሄደ ላለው ዲፕሎማሲያዊ ድርድር እንቅፋት ይሆናል መባሉን “ምከንያታዊ ያልሆነ” ብለውታል።
አምባሳደሩ ጨምረውም “ ጦርነቱ ወደ ሌላ አካባቢ መስፋፋቱ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ወደ ሰፊ ጦርነት እንዲገቡ ይመራል” ብለዋል።
ጦርነቱ ወደ ሌሎች የቀጠናው አካባቢ እንዳይዛመት መከላከል የሚቻለውም በጋዛ ያለውን ጦርነት በማስቆም እንደሆነ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
የአልጀሪያ ከፍተኛ የተመድ ዲፕሎማት አማር ቤንድጃማም “ በሚያሳዝን ሁኔታ የጸጥታው ምክር ቤት በድጋሜ ሳይሳካለት ቀርቷል። ታሪክ ይፋረዳችኋል፤ ህሊናችሁን ፈትሹ” ብለዋል።
የአሜሪካ አጋሮችም ውሳኔዋን ተችተዋል።
የፈረንሳይ የተመድ መልዕክተኛ ኒኮላስ ዲ ሪቪየር፣ በጋዛ ያለውን አስከፊ ሁኔታ በመግለጽ የውሳኔው ሃሳብ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ማዘናቸውን ተናግረዋል።
በተመድ የዋሽንግተን አምባሳደር የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በበኩላቸው በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ድርድር እየተካሄደ ባለበት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ለማቅረብ ትክክለኛው ሰዓት አይደለም ብለዋል።
የዩኬ አቻቸው ባርባራ ውድዋርድም “ ውሳኔው ድርድሩን አደጋ ላይ በመጣል የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚኖረውን ዕድል ይቀንሳል” ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
እስራኤል፣ ሐማስ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የአገሪቷን ድንበር ጥሶ በመግባት ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች ከተገደሉ እና ከ240 በላይ ሰዎች ታግተው ከተወሰዱ በኋላ ነበር በጋዛ ላይ ጥቃት የከፈተችው።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ በከፈተው በዚህ ዘመቻም ከ29 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
አሜሪካ በራሷ ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳብ፣ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግና በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን፣ ታጋቾች እንዲለቀቁ እንዲሁም በጋዛ እርዳታ እንዲደርስ መሰናክሎች እንዲነሱ ይጠይቃል።
አሜሪካ ያቀረበችው ሃሳብ ላይ የጸጥው ምክር ቤት ድምጽ ስለመስጠቱ እንዲሁም መቼ ሊሰጥ እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
ዋይት ሃውስ እስራኤል በራፋህ ላይ ለመፈፀም ያቀደችው የምድር ጥቃት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንደሚያስከትልና በተለይ ግብፅን በመጥቀስ ወደ ጎረቤት አገራት እንዲሰደዱ እንደሚያደርግ ገልጻለች።
ሆኖም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት ግባቸውን እስከሚያሳኩ ድረስ ጦርነቱን ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውንና ምንም ዓይነት ግፊት ይህን አቋማቸውን እንደማይለውጠው ተናግረዋል።
ግማሽ የሚሆነው የጋዛ ሰርጥ ነዋሪዎች ማለትም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን በራፋህ ተጠልለው ይገኛሉ።
ከግብፅ ጋር የምትዋሰነው ደቡባዊቷ ከተማ ከጦርነቱ በፊት 250 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መኖሪያ ነበረች።
አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ አሊያም በድንኳን ውስጥ ያለ በቂ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እና ምግብ ነው ተጠልለው የሚገኙት።
እስራኤል በከተማዋ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የያዘችው እቅድ ወደ አስከፊ ጭፍጨፋ ሊያመራ ይችላል ሲል ተመድ ቀደም ብሎ አስጠንቅቋል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ የሐማስ ተዋጊዎችን ብቻ ኢላማ እንደሚያደርግ ገልጿል።
የእስራኤል ጦርነት የካቢኔ አባል ቤኒይ ጋንትዝ፣ ሐማስ ያገታቸውን እስራኤላውያን እስከ መጋቢት 01/2016 ዓ.ም ድረስ ካልለቀቀ የምድር ጥቃቱ እንደሚከፈት አስጠንቅቀዋል።












