ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በዓለማችን ዝቅተኛ ሰላም ካለባቸው አገራት ተርታ ተመደቡ
በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት ከሰላም አንጻር ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የዓመቱ የዓለም አገራት የሰላም ሁኔታ መዘርዝር አመለከተ።
የአውሮፓውያኑ 2025 ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ (ጂፒአይ) በዓለም ዙሪያ ያሉ የ163 አገራትን የሰላም ሁኔታ በገመገመበት ሪፖርቱ ላይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዝቅተኛ ነጥብ በማግኘት ከዝርዝሩ ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ ከ163 አገራት 25ቱን በመቅደም 138ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ኤርትራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ከፍ ብላ 132ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በተጨማሪም በዚህ የሰላም ሁኔታ ግምገማ ውስጥ ከተካተቱት 44 የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ 36ኛ ስትሆን ኤርትራ ደግሞ 32ኛ ደረጃን ይዛለች።
በዚህም በግምገማው ከተካተቱት አገራት መካከል ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በ2025 ዓለም አቀፉ የሰላም መዘርዝር ውስጥ ዝቅተኛ ሰላም ካለባቸው አገራት ተርታ ውስጥ ተካተዋል።
የዓለም አገራትን የሰላም ሁኔታ የሚያሳየውን መዘርዝር ያዘጋጀው የኢኮኖሚ እና ሰላም ተቋም (አይኢፒ) አይስላንድን በዓለም ሰላም የሰፈነባት አገር በማለት ቀዳሚ አድርጓታል።
የዓለም የሰላም መዘርዝር የዓለም አገራትን ሰላም 23 አመላካቾችን ተጠቅሞ የአገራትን የፀጥታ እና የመረጋጋት ሁኔታ ይመዝናል።
ይህ የአገራት የሰላም ሁኔታ ደረጃ የሚወጣው አገራቱ ካላቸው ማኅበረሰባዊ ደኅንነት፣ ከለባቸው የአገር ውስጥ እና የውጭ ግጭት እና ከሚያካሂዱት ወታደራዊ ግንባታ አንጻር ነው።
የ2025 የዓለም የሰላም መዘርዝር ሪፖርት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ሰላም ላይ የታዩ ጉልህ ፈተናዎችን አስቀምጧል።
በ2020 መገባደጃ ላይ በተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ በተለይም በትግራይ ክልል ውስጥ በተከሰተው ጦርነት የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሰላም ማሽቆልቁሉን ሪፖርቱ አስታውሷል።
ይህ ግጭት እንደ ኦሮሚያ እና አማራ ባሉ አካባቢዎች ከተከሰቱ አለመረጋጋቶች ጋር ተዳምሮ ለጅምላ መፈናቀል፣ ሰብዓዊ ቀውሶች እና መጠነ ሰፊ የፀጥታ ችግር አስከትሏል፤ ይህም የአገሪቱን መረጋጋት እና ሰላም በእጅጉ ጎድቷል።
ከትጥቅ ግጭቶች ባሻገር፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሰላም ደረጃዋ ዝቅተኛ መሆን አስተዋፅኦ ያደረገ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ግጭቱን ለመፍታት የተኩስ አቁም እና ድርድርን ጨምሮ ሌሎች የተደረጉ ጥረቶች ደካማ እና ያልተጠናቀቁ መሆናቸውንም በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሰላማዊ ድርድር ላይ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም የውስጥ ልዩነቶችን በመቆጣጠር፣ በየአካባቢው ያሉ ግጭቶችን መፍታት እና ዘላቂ መረጋጋትን ማረጋገጥ ባለመቻሉ አገሪቱን ለከፍተኛ የግጭት ስጋት እንድትጋለጥ እያደረጋት ነው ሲል አስፍሯል።
ኤርትራም በተመሳሳይ አገሪቱን ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በበላይነት በመራው አምባገነናዊ አስተዳደር እና በመካሄድ ላይ ባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተነሳ በዓለም የሰላም መዘርዝር (ጂፒአይ) ላይ ደካማ አፈጻጸም አሳይታለች።
አገሪቱ በዓለም ላይ ካሉት እጅግ አፋኝ አገራት አንዷ ሆና መቀጠሏን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ የፖለቲካ ነፃነቶች ውስንነት፣ የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት እና የዘፈቀደ እስር በስፋት በአገሪቱ ውስጥ እንደሚታይ አስፍሯል።
እነዚህ የውስጥ ፖሊሲዎች ለዲሞክራሲ ማሻሻያ ወይም ለሕዝቡ የላቀ ነፃነት የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት በማደናቀፍ፣ በሥልጣን ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ለቀጠለው ዝቅተኛ የሰላም ውጤት አስተዋፅዖ አድርገዋል።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን በመሰለፍ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ ገብታ የነበረ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰላም መመዘኛ ዝቅተኛ ነጥብ እንድታስመዘግብ አድርጓታል።
በ2018 በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የድንበር ውዝግቦቻቸውን በመደበኛነት ቢፈታም የሁለቱን አገራት ውጥረት ግን የሰሜን ኢትዮጵያን ደም አፋሳሽ ጦርነት ካስቆመው ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ እያተባባሰ ይገኛል።
የኤርትራ ከሌላው ዓለም መነጠል፣ ያላት ወታደራዊ ተሳትፎ እና ከሰብዓዊ መብት ረገጣ ጋር ተዳምሮ አገሪቱ በአገር ውስጥም ሆነ በቀጠናው ሰላም እና ደኅንነት ላይ ለውጥ እንዳታሳይ ማድረጉ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ሌሎች የአፍሪካ አገራት እና ሰላም
በግሎባል ፒስ ኢንዴክስ መስፈርቶች ከአፍሪካ አገራት 26ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ሰላም የሰፈነባት አገር የተባለችው ሞሪሺየስ ስትሆን እርሷን በመከተል በአህጉሪቱ በፖለቲካ መረጋጋት እና ዝቅተኛ የሆነ ግጭት በማስመዝገብ ቦትስዋና፣ ናሚቢያ እና ጋምቢያ ይከተላሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2025 የዓለም ሰላም መዘርዝር 97 የዓለም አገራት ሰላም ያሽቆለቆለባቸው ተብለው ተፈርጀዋል።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የሰላም ማሽቆልቆል ተመዝግቧል።
በዚህ የዓለማችን ክፍል ውስጥ ካሉት አገራት ግማሽ ያህሉ በአጠቃላይ ሰላማቸው የተሻሻለ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ገሚሶቹ ደግሞ ሰላም ርቋቸዋል።
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት አማካይ የሰላም ነጥብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ0.17 በመቶ ቀንሷል።
ካለፉት 5 ዓመታት ወዲህ ከ44 የአፍሪካ አገራት ውስጥ 36ቱ በአንድም ወይም በሌላም መንገድ ግጭት ውስጥ ገብተው እንደነበር ሪፖርቱ ተመልክቷል።
በዓለም አቀፉ የሰላም መዘርዝር ውስጥ ከተቀመጡት ሰላማቸው ካሽቆመለቆ አስር አገራት መካከል ሦስቱ በአፍሪካ ውስጥ ይገኛሉ።
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በርካታ የፀጥታ ቀውሶች፣ የፖለቲካው አለመረጋጋት መጨመር በተለይም በማዕከላዊ የሳህል አካባቢ አለመረጋጋት እና ሽብርተኝነት አጋጥሟል።
ቡርኪና ፋሶ በዓለም ላይ ከፍተኛው የሽብርተኝነት ስጋት ያለባት አገር መሆኗ በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከዓለማችን አስር የሽብርተኝነት ስጋት ካለባቸው አገራት መካከልም ስድስቱ የሚገኙት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ነው።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቀጠናው ዝቅተኛ ሰላም ካለባቸው እና ሰላም በአስከፊ ሁኔታ ካሽቆለቆለባቸው አገራት መካከል ተመድባለች።
ይህች አገር በ2025 የዓለም ሰላም መዘርዝር ውስጥ ከአምስቱ ዝቅተኛ ሰላም ካለባቸው አገራት መካከል አንዷ ሆና ተቀምጣለች።
ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጎን ሰላማቸው ያሽቆለቆለ ተብለው የተመዘገቡ የዓለማችን አራት አገራት ባንግላዲሽ፣ ዩክሬን፣ ሩሲያ እና ምያንማር ናቸው።
በተቃራኒው ኡጋንዳ ደግሞ በአፍሪካ ውስጥ በሰላም ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየች መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
መካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ በ2025 በዓለም ላይ በጣም ዝቅተኛ ሰላም ያለባቸው ቀጠናዎች ተብለዋል።
ሱዳን፣ የመን፣ ሶሪያ እና እስራኤል በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላም ካጡ 10 አገራት መካከል ተቀምጠዋል።
የዓለማችን ሰላማዊ አገራት
በርካታ ግጭቶች በተከሰቱበት በዚህ የፈረንጆች አንድ ዓመት ውስጥ አምስት አገራት በዓለም እጅግ ሰላማዊ ከሆኑ አገራት ተርታ ተመድበዋል።
አይስላንድ፣ አየርላንድ፣ ኒውዚላንድ፣ ኦስትሪያ እንዲሁም ስዊትዘርላንድ የዓለማችን ሰላማዊ አገራት ተብለው ከአንድ እስከ አምስት በቅደም ተከተል ከተቀመጡት አገራት መካከል ናቸው።
አይስላንድ ከአውሮፓውያኑ 2008 ጀምሮ በዓለም ዙሪያ በጣም ሰላማዊ አገር የሚለውን ማዕረግ ይዛ ቀጥላለች።
በ2025 ዓለም አቀፍ ጦርነቶች እየተባባሱ፣ አገራት ድንበሮቻቸውን እየዘጉ እንዲሁም የንግድ ውጥረቶች ተባብሰው ታይተዋል።
በ2025 ዓለም አቀፍ የሰላም መዘርዝር (ጂፒአይ) መሠረት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በመንግሥታት መካከል የተካሄዱ ግጭቶች ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ብዙ አገሮች ወታደራዊ ኃይሎቻቸውን ሲያጠናክሩ እና ለመከላከያ የሚያወጧቸውን ወጪዎች ጨምረው ታይተዋል።
በዚህ መዘርዝር ላይ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ከተሰለፉት አገራት መካከል የተወሰኑት አገራት ላለፉት ሁለት አስርታት በመረጋጋት፣ በሰላም ፖሊሲዎች ረገድ ወጥ አቋም ያሳዩ አገራት ሆነዋል።
በዓለም የሰላም መዘርዝር ውስጥ ግርጌው ላይ የተቀመጡት ሩሲያ እና ዩክሬን ሲሆኑ፣ ሁለቱም ላለፉት ሦስት ዓመታት በዘለቀ ጦርነት ውስጥ ናቸው።