ፕሬዝደንት ኢሳያስ ኢትዮጵያ 'ከጠብ አጫሪነት ይልቅ በውስጥ ችግሮቿ ላይ ታተኩር' ሲሉ ተናገሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከአገራቸው ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ጎረቤታቸው ኢትዮጵያ ከምታሰማው የጠብ አጫሪነት ንግግር ተቆጥባ በአንገብጋቢ የውስጥ ችግሮቿ ላይ ታተኩር ሲሉ ተናገሩ።

ፕሬዝደንቱ ይህንን የተናገሩት ትናንት ረቡዕ ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም. ከአገራቸው ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢው ጋር ባደረጉት ሁለተኛ ክፍል ቃለ ምልለሳቸው ነው።

ባለፈው ቅዳሜ በቀረበው ክፍል አንድ ላይ በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው ውዝግብ አንስተው የነበረ ሲሆን፣ በሁለተኛው ክፍል በኤርትራ የውስጥ ጉዳዮች ያተኩራሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም ሰፊ ሰዓት ሰጥተው ስለ ጎረቤት አገር ሱዳን እንዲሁም ስለ የተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ እና ሌሎች ጉዳዮች ተናግረዋል።

ፕሬዝደንቱ በዚሁ ንግግራቸው ኢትዮጵያን በመጥቀስ ጠብ አጫሪ ንግግሮችን ከመስማት ይልቅ አንገብጋቢ የውስጥ ችግሮቿን ለመፍታት ትኩረት እንድታደርግ በድጋሚ አሳሰበዋል።

ፕሬዝደንቱ በመጀመሪያው ክፍል ቃለ ምልልስ ላይም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት የላከችውን ደብዳቤ ጠቅሰው "አስገራሚ የውሸት ክስ" በማለት ማጣጣላቸው ይታወሳል።

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቅዳሜ ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም. በሰጡት የመጀመሪያ ክፍል ቃለ ምልልስ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ መንግሥትን ከስሶ ለተባበሩት መንግሥታት ያስገባውን ደብዳቤ 'ርካሽ ውሸት' ሲሉ አጣጥለው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ክስ "የብልጽግና ፓርቲ የሚያደርገውን የጦርነት ዝግጅት ለመሸፈን ያቀረበው ርካሽ ውሸት ነው" ብለው ነበር።

ትናንት ረቡዕ ምሽት በተላለፈው ሁለተኛው ክፍል ቃለ ምልልሳቸው ላይም አገራቸው የጦርነት ፍላጎት እንደሌላት ተናግረዋል።

"የአዲስ አበባው መንግሥት ሌሎች ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉት፤ መስራት ከፈለገ። ማስቀደም ያለበት ጉዳይ ትቶ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ ገብቶ አለመረጋጋት የሚፈጥርበት ምክንያት ምንድን ነው? አያስፈልግም" ሲሉም ተደምጠዋል።

በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ላይ "ኤርትራን መወንጀል ሌላ ጣጣ ማምጣት ነው" ያሉት ፕሬዝደንቱ "የከፋ ውጤት ከመጣ ማቆም አይቻልም። አሁኑኑ አስቁሙ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንቱ "ዲፕሎማሲ . . . በአጋጣሚዎች ድግስ ላይ ስትገናኝ ሰላም ሰላም ስለተባባልክ፣ ፎቶግራፍ ስለተነሳህ አይደለም። እንደዚህ ያሉ አደጋዎች ሲመጡ አይሆንም፤ አያስፈልግህም ስትል፣ እዚህ ላይ ነው ዲፕሎማሲ መስራት ያለብህ" ብለዋል።

ኤርትራ ጦርነት ለማድረግ እየተዘጋጀች ነው የሚለውን ክስ በመጥቀስም "ስም ማጥፋት ነው። ዋሽተህ ማሳሳት የለብህም። ነገ ሌላ ችግር ሲመጣ፣ ያን ችግር ማጋነን ተገቢ አይደለም። ችግር ሳይመጣ ግን ማስቆም አለብህ" ብለዋለ።

ይሄ ሁሉ ቀጣናውን እያመሰች ያለችውን ኤማሬትስ ነች ሲሉ የከሰሱት ፕሬዝደንቱ፣ "ከኤምሬትስ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ እየተጓዘ ያለውን መሳሪያ እያየን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ይሄ በባሕር ሳቢያ እየተባለ ያለውን የብልጽግና አጀንዳ አይደለም" ሲሉ የተናገሩት የኤርትራው ፕሬዝደንት "ሥራቸውን መሥራት አለባቸው" ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ ሌሎች ቀጣናውን ይበጠብጣሉ በማለት እስራኤልን፣ ፈረንሳይን እና አሜሪካንንም ከስሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ በመጀመርያው ቃለ ምልሳቸው ወቅት ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ቢናገሩም አሁን ግን ቀጠናውን ከሚያምሱ አገራት መካከል ጠቅሰዋታል።

ቅዳሜ ምሽት በተላለፈው ቃለ መጠይቃቸው ላይ የኤርትራ እና የአሜሪካን የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተመለከተ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ኤርትራ ላለፉት ሀምሳ ዓመታት በዋሽንግተን ሲደርስባት የነበረውን በደሎች ሁሉ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ወዲያውኑ "ለመርሳት እና ይቅር ለማለት" መወሰኗን ተናግረው ነበር።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በባይደን አስተዳደር እንቅፋት የገጠመውን የአገራቱን ግንኙነት ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ለማደስ ማሰባቸውን ተናግረው ነበር።

ፕሬዝደንቱ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘውን ሱዳንን በተመለከተ ባላት ወሳኝ ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ የተነሳ የረጅም ጊዜ ፍላጎት ባላቸው የውጭ ኃይሎች አማካይነት ግጭቱ ተባብሷል ብለዋል።

የኤርትራው መሪ በዚሁ ቃለምልሳቸው ላይ "በዚህም ከስዊዝ እስከ ኤደን ባሕረ ሰላጤ እና እስከ ታንዛኒያ ድረስ ያሉትን ወደቦች የመቆጣጠር ሰፋ ያለ እና ግራ አጋቢ አጀንዳ ውስጥ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ግንባር ቀደም ናት" ብለዋል።

ይህ አጀንዳም የኢምሬትስ መሥራች አባት እና ታላቅ መሪ ከነበራቸው ዕቅድ ተቃራኒ ነው ያሉት ኢሳያስ፣ ነገር ግን ከጀርባ ሆነው ሙሉውን ዕቅድ የሚያንቀሳቅሱ ሌሎች ኃይሎች ስላሉ የወቅቱ የኤሚሬትስ መሪ አጀንዳ ብቻ ነው ሊባል አይችልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን ይፋ ካደረገች በኋላ ተሻሽሎ የነበረው የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ሻክሮ አሁን ወደ መካሰስ ደርሷል።

ሁለቱ አገራት አገራት መካከል የሚሰማው መካሰስ እና የቃላት ልውውጥ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል። አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በሁለቱም ወገን ወታደራዊ ዝግጅት እየተካሄደ ነው።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በሌሎች ጉዳዮች ምን አሉ?

ፕረዚደንት ኢሳይያስ በረቡዕ ምሽት ቃለ ምልልሳቸው መግቢያ ላይ፣ ስለ ሱዳን እና ስለ አገራቸው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በሠፊው ተናግረው ነበር።

በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከግማሽ ሰዓት በላይ ያወሩ ሲሆን "ሱዳን ውስጥ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት አይደለም፤ ወረራ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ኢሳያስ በመቀጠል ሱዳን የውጭ ኃይሎች ወረራ ሰለባ ሆናለች በማለት፣ በዋናነት በስፋት እንደሚባለው የሁለቱ ጄኔራሎች ጦርነት ሳይሆን (አል ቡርሃን እና ሄሜቲ) የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጣልቃ ገብነትን መሆኑን በማንሳት ወቅሰዋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሁሉም የቀጣናው አገራት ማለትም፣ በሊቢያ፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ መካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ እና ደቡብ ሱዳን እየወሰደች ያለው እርምጃ ከማንም የተሰወረ አይደለም ሲሉም አክለዋል።

በእነዚህ መስመሮች የጦር መሳሪያ እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እያቀበለች ነው ሲሉ ወንጅለዋል።

ኤርትራ በጄኔራል አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ኃይልን ትደግፋለች። ሆኖም ፕሬዚዳንቱ በጉዳዩ ላይ በግልጽ የሰጡት አስተያየት የለም።

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ሁሉም ጎረቤት አገራት በአንድም ሆነ በሌላበኩል ተሳታፊ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።

ፕሬዚዳንቱ የማኅበራዊ አገልግሎትን በተመለከተ ሲናገሩ "በጎዳና ላይ ተኝተው፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ፣ በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙ የተጎሳቆሉ እና ምስኪን የሚባሉ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ ነው" ብለዋል።

ችግሩ ገና በወጣትነት ጊዜ ሊፈታ ይገባል እንጂ "ገንዘብ፣ ስጦታ በመስጠትና እርዳታ በማስለመድ" አይደለም ብለዋል።

"ተጨቆኑ የሚባሉት የአካል፣ የአዕምሮ ጉዳተኞች፣ ሥራ አጦች ቋሚ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ሲሉም አክለዋል።

ይኹን እንጂ አስተዳደሮቹ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ካልሆነ በስተቀር እንዴት እንደሚተገበር ወይም የጊዜ ገደብ አላስቀመጡም።