በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች የኢራቅን ምክር ቤት ጥሰው ገቡ

ተቃዋሚዎቹ ምክር ቤቱ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሲዘፍኑ፣ ሲደንሱ፣ ጠረጴዛ ላይ ተኝተውም ታይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢራቃውያን ተቃዋሚዎች በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቀውን የአገሪቱን ምክር ቤት ጥሰው ገቡ።

ባግዳድ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ቤት ጥሰው የገቡት ሙቅታዳ አል-ሳድር የተባሉ የሃይማኖት መሪ ደጋፊዎች ናቸው።

የእኚህ የሃይማኖት መሪ ተቀናቃኝ የሆኑ ግለሰብ ለጠቅላይ ሚኒስተርነት መታጨታቸውን በመቃወም ነው ደጋፊዎቻቸው ምክር ቤቱን ጥሰው የገቡት።

የሳድር ፖለቲካዊ ጥምረት ባለፈው ጥቅምት በተካሄደው ምርጫ አብላጫ ድምጽ ቢያገኝም፣ ምርጫውን ተከትሎ በተነሳው ፖለቲካዊ ውጥረት ሳቢያ ሥልጣን አልያዘም።

ፖሊሶች ተቃዋሚዎቹ ላይ አስለቃሽ ጭስ እና ውሃ መተኮሳቸው ተዘግቧል።

ተቃዋሚዎቹ ምክር ቤቱን ጥሰው ሲገቡ የሕዝብ እንደራሴዎች በቦታው አልነበሩም።

ተቃዋሚዎቹ የጣሱት ባግዳድ ውስጥ የሚገኘው ግሪን ዞን የተባለው አካባቢ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግለታል።

የአገሪቱን ምክር ቤት ጨምሮ ኤምባሲዎችና ሌሎችም ቢሮዎች የሚገኙበት አካባቢ ነው።

የፀጥታ ኃይሎች መጀመሪያ አካባቢ ተቃዋሚዎቹን ማስቆም ቢችሉም ኋላ ላይ ግን ተቃዋሚዎቹ ምክር ቤቱን ጥሰው እንደገቡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል የፀጥታ ምንጮቹን ጠቁሞ ዘግቧል።

ተቃዋሚዎቹ ምክር ቤቱ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሲዘፍኑ፣ ሲደንሱ፣ ጠረጴዛ ላይ ተኝተውም ታይተዋል።

የኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል-ካዲሚ ተቃዋሚዎቹ ከምክር ቤቱ እንዲወጡ ጠይቀዋል።  

ተቃውሞው የመጣው ላለፉት ዘጠኝ ወራት የነገሠውን ውጥረት ተከትሎ ነው።

በአገሪቱ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ባለመስማማታቸው አዲስ መንግሥት መመሥረት አልተቻለም።   

የሺአ መምህሩ ሳድር በኢራቅ የአሜሪካንን ጣልቃ ገብነት ይቃወማሉ።

ኢራቅን ባማከለ ብሔርተኛ አስተሳሰባቸው የጥቅምቱን ምርጫ እንዳሸነፉ ተናግረዋል።

ነገር ግን ከተቃዋሚዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣ በእሳቸው የሚመራው ጥምረት አዲስ መንግሥት መመሥረት አልቻለም።

ደጋፊዎቻቸው፣ ከኢራን ጋር ቅርበት አላቸው ብለው የሚወቅሷቸው ሞሐመር አል-ሱዳኒ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት መታጨታቸውን ተቃውመዋል።

ባግዳድ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ቤት ጥሰው የገቡት ሙቅታዳ አል-ሳድር የተባሉ የሃይማኖት መሪ ደጋፊዎች ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በነዳጅ ሀብት የምትታወቀው ኢራቅ፣ ፈርጀ ብዙ መሰናክል ገጥሟታል።

ሕዝቡ ሙስና፣ ሥራ አጥነት እና የሕዝብ አገልግሎት መጓተትን በመቃወም እአአ በ2019 ለተቃውሞ አደባባይ መውጣቱ ይታወሳል።

በወቅቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች እንደተገደሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዋች ተናግሯል።

የሳድር ደጋፊዎች በ2016ም ምክር ቤት ጥሰው ገብተው ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የኢራቅ ልዑካን ቡድን የኢራቅ ሕዝብ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ተቃውሞውን የመግለጽ መብት አለው ሲል መግለጫ አውጥቷል።