ኮሮናቫይረስ መጀመሪያ በተመዘገበባት ውሃን የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኮሮናቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በተመዘገበባት የቻይናዋ ውሃን ከተማ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለባቸው።
አራት ምልክት የሌለባቸው ሰዎች ቫይረሱ ስለተገኘባቸው በጂያንግሺያ አካባቢ ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው ወይም በግቢያቸው ለሦስት ቀናት እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል።
ቻይና “ዜሮ ኮቪድ” የሚል ስትራቴጂ ትከተላለች። ለዚህም በሰፊው መመርመር፣ ጥብቅ ልየታ እና የእንቅስቃሴ ገደብን ትተገብራለች።
ይህም ከሌሎች አገራት ያነሰ የሞት ቁጥር እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል።
ግለሰቦች እና የንግድ ተቋማት በተደጋጋሚ በሚገጥማቸው እገዳ ምክንያት ስትራቴጂው ተቃውሞ እየበረታበት ነው።
12 ሚሊዮን ነዋሪዎች ባሉባት ውሃን ከሁለት ቀናት በፊት በተካሄድ መደበኛ ምርመራ ሁለት ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
ሁለት ሰዎች ደግሞ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ባላቸው ንክኪ ተለይተዋል። ይህን ተከትሎም በፍጥነት የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል።
ሳይንቲስቶች ኮሮናቫይረስን መጀመሪያ ያገኙባት ቦታ በመሆኗ ውሃን እአአ በ2020 በመላው ዓለም ታዋቂ ለመሆን በቅታለች።
ከባድ የእንቅስቃሴ ገደብ ከተጣለባቸው ከተሞችም ቀዳሚዋ ናት።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በወቅቱ በተላለፈው ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ዓለም ጉድ ተሰኝቶ ነበር። በኋላ ግን አገራት ተመሳሳይ እገዳ ለመጣል ተገደዋል።
በኋላም ቻይና ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ስኬታማ ለመባል በቃች። የተጣሉት እገዳዎችም ከብዙ አገራት ቀድመው ተነስተዋል።
ይህም ግን በፍጥነት ተቀየረ።
የቻይና “ዜሮ ኮቪድ” የተሰኘው ስትራቴጂ በተደጋጋሚ የእንቅስቃሴ ገደብ ለመጣል ምክንያት ሆነ። ይህም ሌሎች አገራት ከቫይረሱ ጋር አብሮ ለመኖር ከሚያደርጉት ጥረት ጋር የሚቃረን ነው።
25 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባት እና የቻይና የፋይናንስ ማዕከል የምትባለው ሻንጋይ ባለፈው ሳምንት ነው ከሁለት ወር የእንቅስቃሴ ገደብ የወጣችው።
የቻይና ኩባንያዎች ይህንን ሁኔታ ለማለፍ ሠራተኞቻቸውን በፋብሪካዎች አቆይተው ማሠራትን መርጠዋል።
በቻይናዋ ውሃን የሚገኘው ሁዋናን የባሕር ምግቦች እና የዱር እንስሳት ሥጋ ገበያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማዕከል እንደነበረ የሚያሳይ “አሳማኝ ማስረጃ” አለ ሲሉ ተመራማሪዎች ከሰሞኑ ገልጸዋል።
ሁለት ጥናቶች በቻይናዋ ከተማ ከመጀመሪያው ወረርሽኝ የተገኘውን መረጃ እንደገና መርምረዋል።
ከጥናቶቹ አንዱ እንደሚያሳየው ቀደም ብለው የታወቁ የቫይረሱ መነሻዎች በገበያው ስፍራ በብዛት ተገኝተዋል።
ሌላው ጥናት የወረርሽኙን የመነሻ ጊዜ ለመለየት የዘረ መል መረጃን ተጠቅሟል።
እአአ በኅዳር ወይም በታኅሣሥ 2019 መጀመሪያ ላይ ወደ ሰዎች የተላለፉ ሁለት የበሽታው ዝርያዎች እንዳሉም ተጠቁሟል።
ተመራማሪዎቹ በጋራ እንደገለጹት ይህ ማስረጃ ሳርስ-ኮቭ-2 በ2019 መጨረሻ በሁዋናን ገበያ በተሸጡና በሕይወት ባሉ አጥቢ እንስሳት ላይ ይገኝ እንደነበር ያሳያል ብለዋል።
በሁለት የተለያዩ “ክስተቶች” ቫይረሱ ካለበት እንስሳ በገበያው ወደሚሠሩ ወይም ወደሚገዙ ሰዎች ተላልፏል ብለዋል።
ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑትና በግላስጎው ዩኒቨርሲቲ የቫይረስ ተመራማሪ በመሆን የሚያገለግሉት ፕሮፌሰር ዴቪድ ሮበርትሰን፣ ጥናቶቹ “ቫይረሱ ከላብራቶሪ መጣ የሚለውን የሐሰት ዘገባ ያስተካክላል” የሚል እምነት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።












