ኢትዮጵያ ወደ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ለመመለስ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር የሚደረገውን የሦስትዮሽ ድርድርን መልሳ ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን ገለጸች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋው የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ከሆኑት ማይክ ሐመር ጋር በተወያዩበት ጊዜ ነው የአገራቸውን ፍላጎት የገለጹት።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ አምባሳደር ምስጋኑ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር የሚካሄደውን የሦስትዮሽ ድርድርን መልሳ ለመጀመር ዝግጁ ናት” ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።
ኢትዮጵያ በመጪዎቹ የክረምት ወራት ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት ሊጠናቀቅ የተቃረበውን ግድብ በውሃ ለመሙላት እየተዘጋጀች ሲሆን፣ ግብፅ የውሃ ሙሌቱን እና የግድቡ ቀጣይ የሥራ ሁኔታ ላይ ስምምነት እንዲደረግ ትፈልጋለች።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ግብፅ፣ ኢትዮጵያ ድርድር ተደርጎ ስምምነት ሳይደረስ ግዙፉን ግድብ በውሃ መሙላቷን ለመቀጠል ድርድሩን “ለጊዜ መግዣነት እየተጠቀመችበት ነው” ስትል መክሰሷ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ መጀመሯን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ከግብፅ እና ከሱዳን በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማት ሲሆን፣ የግድቡ ጉዳይም ከአፍሪካ ኅብረት ባሻገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ሦስቱ አገራት በግድቡ ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት በአፍሪካ ኅብረት እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ንግግር ቢያደርጉም ሁሉንም ከሚያግባባ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቆይተዋል።
ተጠናቆ ሥራውን ሲጀምር በአፍሪካ ግዙፉ እንደሆነ የሚነገርለት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አገሪቱ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ከራሷ በማውጣት እያከናወነች ነው።
በአፍሪካ ትልቁ የሚባለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን እየገነባች ያለችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ግድቡን በውሃ ስትሞላ ቆይታለች።
ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግዙፍ ግድብን በውሃ መሙላት ከመጀመሯ በፊት አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት በማለት ሲወተውቱ ቢቆዩም፣ ኢትዮጵያ ሳትቀበለው ለሦስት ዙር ግድቡ ውሃ እንዲይዝ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በግድቡ ዙሪያ እየተጀመረ ሲቋረጥ የቆየ ድርድር ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ ሱዳን እና ግብፅ የግድቡን የውሃ ሙሌት እና ቀጣይ ሥራን በተመለከተ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ግን በሁለቱ አገራት በኩል የሚቀርቡ የስምምነት ሐሳቦች አብዛኛው ውሃው ከግዛቷ የሚመነጨውን የአባይ ወንዝን በሚያስፈልጋት ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳታውል የሚገድብ ነው ስትል ሳትቀበለው ቀርታለች።
ግንባታው ከተጀመረ ከአስር ዓመት በላይ የሆነው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ 90 በመቶው መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለጎረቤት አገራት ኃይል ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።












