ጠ/ሚ ዐቢይን ጨምሮ የአፍሪካ መሪዎች ማክሮንን እንኳን ደስ አለዎት ብለዋል

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ መሪዎች ኢማኑኤል ማክሮን በድጋሚ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

ማክሮን ትናንት በተደረገ አገር አቀፍ ምርጫ ተቀናቃኛቸው ማሪን ሌ ፔንን በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋቸዋል፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ከማክሮን ውጭ ለሁለተኛ ጊዜ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሆኖ የተመረጠ መሪ አልነበረም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው "ወዳጄ ኢማኑኤል ማክሮን ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠህ ታሪክ በመሥራትህ እንኳን ደስ አለህ! በአገራችን መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለው ጽፈዋል።

ማክሮን ቀኝ አክራሪዋን ማሪን ሌ ፔንን ማሸነፋቸው በአውሮፓ ኅብረት አባላት ዘንድ እፎይታን መፍጠሩ ተዘግቧል።

ሌ ፔን ስደተኞችን የማባረር፣ ፈረንሳይን ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እንዲሁም ከአውሮፓ ኅብረት የማስወጣት ዕቅድ እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።

ማክሮን ያሸነፉት ከድምጽ ሰጪው ሕዝብ 58.55 ከመቶ በማግኘት ሲሆን፣ ሌ ፔን ድምጽ ማግኘት የቻሉት ግን 41.45 የሚሆነውን ብቻ ነው።

ለማክሮን የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክት ካስተላለፉ አፍሪካውያን መሪዎች መካከል የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር የሆኑት የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ይገኙበታል።

የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜም በትዊተር ገጻቸው ላይ "የማክሮን አመራር ከክፍፍል ይልቅ አንድነትን ያሰፍናል" ብለዋል።

ማክሮን ከድል በኋላ ባደረጉት ንግግር የተከፋፈለውን የፈረንሳይ ሕዝብ አንድ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

ማክሮን በተለይም በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች ዘንድ ሲተቹ ቆይተዋል። የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር አለመቻላቸውም ከፍተኛ ተቃውሞን አስነስቶባቸዋል፡፡

የምርጫ ውጤቱ ይፋ ከሆነ በኋላ ሌ ፔን ሽንፈታቸውን የተቀበሉ ሲሆን ያገኙት ድምጽ በራሱ ለፓርቲያቸው ትልቅ ድል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡