ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ክርስቲያኖ ሮናልዶ የደጋፊ ስልክ ሰብሯል መባሉን ተከትሎ ጉዳዩ በፖሊስ እየተመረመረ ነው
የማንቸስተር ዩናይትድ የፊት መስመር ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ የተመልካችን ስልክ ሰብሯል መባሉን ተከትሎ የመርሲሳይድ ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረው እንደሆነ አስታውቋል።
ባሳለፍነው ቅዳሜ ማንቸስተር ዩናይትድ በኤቨርተን አንድ ለባዶ መሸነፉን ተከትሎ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የአንድ ተመልካችን ስልክ መስበሩ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ከክስተቱ በኋላም ሮናልዶ ይቅርታ ጠይቋል።
የመርሲሳይድ ፖሊስ ቅዳሜ ዕለት በጉዲሰን ፓርክ ስታዲየም ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃት እየመረመርኩ ነው ብሏል።
የፖሊስ ቃል አቀባይ እንዳስታወቀው ጉዳዩን ለመመርመር ከማንችተር ዩናይትድና ከኤቨርተን እግር ኳስ ክለቦች ጋር በትብብር እየተሠራ ነው።
"ተጫዋቾች ሜዳውን ለቅቀው በሚሄዱበት ወቅት አንድ ታዳጊ በተቃራኒ ቡድን አባል ጥቃት ደርሶበታል። ስልኩም ጉዳት ደርሶበታል" ብሏል ፖሊስ።
"መመለስ የሚገባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ መረጃ እያሰባሰብን ነው። በስታዲየሙ ውስጥ ያሉ ተንቀሳቃሽ ምስል የሚያስቀሩ ካሜራዎችን ለመመልከት ከኤቨርተን ጋር እየሠራን ነው። ምስሎቹን ካገኘንና በቦታው የነበሩ የአይን እማኞችን ካነጋገርን በኋላ በትክከል ምን እንደተፈጠረ ማቀው እንችላለን።"
ፖሊስ አክሎም በጉዳዩ ላይ ማንኛውም አይነት መረጃ ያለው ሰው የመርሲሳይድ ፖሊስን እንዲያነጋግርና እንደ ፌስቡክ እና ትዊተር ባሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩልም መረጃዎችን እንዲያጋሩ ጠይቋል።
ማንችስተር ዩናይትድ በበኩሉ ስለተፈጠረው ነገር መረጃው እንዳለውና በማንኛውም ጉዳይ ከፖሊስ ጋር ለመተባበር ዝግጁ እንደሆነ አስታውቋል።
ማንችስተሮች ቅዳሜ በኤቨርተን አንድ ለባዶ መሸነፋቸውን ተከትሎ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ለመሳተፍ ያላቸውን ዕድል በእጅጉ ያጠበበው ሲሆን፣ ኤቨርተን ደግሞ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገውን ጉዞ ያሳመበረበትን ሶስት ነጥብ አግኝቷል።
"በእንደዚህ አይነት ወቅት ስሜትን መቆጣጠር በጣም ከባድ ነው" ብሏል ሮናልዶ።
አክሎም "ነገር ግን ሁሌም ቢሆን ለሁሉም ሰው ክብር ማሳየት አለብን። ታጋሽና ለሌሎች ምሳሌ የሚሆኑ ነገሮችን ማድረግ አለብን በተለይ እግር ኳስን ለሚወዱ ወጣቶች። በወቅቱ ስሜቴን መቆጣጠር ባለመቻሌ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለው። ጥሩ የስፖርታዊ ጨዋነት ለማሳየት በቁጣ ስሜቴን የገለጽኩበት ተመልካች በኦልድ ትራፎርድ ተገኝቶ ጨዋታ እንዲመለከት ለማድረግ እፈልጋለው" ብሏል ሮናልዶ ይቅርታ በጠየቀበት የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ።