አል-ሸባብ የሶማሊያ መሪዎችን ዒላማ ስለማድረጉ የደኅንነት ምንጮች አስታወቁ

ታትሟል

ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው እና በሶማሊያ በስፋት የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛው ታጣቂ ቡድን፣ አል-ሸባብ የሶማሊያ መሪዎችን ዒላማ ስለማድረጉ የደኅንነት ምንጮች አስታወቁ።

የሶማሊያ የደኅንነት ኤጀንሲ የአገሪቱ ፕሬዝደንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር የሽብር ቡድኑ ዒላማ ውስጥ መግባታቸውን አስታውቋል።

ብሔራዊ የመረጃ እና የደኅንነት ኤጀንሲ በትዊተር ገጹ ላይ ታጣቂ ቡድኑ በአገሪቱ መሪዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ስለሸረበው ሴራ ለመሪዎች አስውቄያለሁ ብሏል።

ኤጀንሲው በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም፤ ፕሬዝደንት ሞሐመድ ፈርማጆን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሴን ሮብሌን ለመግደል በተሸረበው ሴራ ተሳታፊ የሆኑትን እያደንኩ ነው ብሏል።

ይህ የኤጀንሲው ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ሶማሊያ የዘገየ ምርጫ ማካሄድ ተስኗት ፖለቲካዊ ውጥረቱ ባያለበት ወቅት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም አል-ሸባብ በሶማሊያ የሚያደርሰውን ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሏል። በቅርቡ አል-ሸባብ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል።

ይህ አየር ማረፊያ የተባበሩት መንግሥታት ቢሮዎች፣ የኤምባሲዎች እና ሚሲዮኖች መገኛ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም አል-ሸባብ በቅርቡ በሶማሊያ ማዕከላዊ ቤሌደዌይኔ ተብላ በምትጠራ ከተማ ባደረሰው ሁለት የአጥፍቶ ማጥፋት ጥቃቶች 48 ሰዎች ተገድለዋል።

ከሟቾቹ መካከል አንዷ የአገሪቱ የፌደራል ፓርላማ አባል ናቸው።