በኦሮምኛ እና በአማርኛ ቋንቋ የተመደረከው የ'አባ ጅፋር ለመፎ' ቴአትር

አባ ጅፋር ለመፎ በመድረክ ላይ
ታትሟል

'አባጅፋር ለመፎ' በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ቴአትር በትናንትናው ዕለት፣ እሁድ፣ አዲስ አበባ በሚገኘው ብሔራዊ ቴአትር ለእይታ በቅቷል።

ይህ ቴአትር፣ ተጽፎ የተዘጋጀው፣ በጅማ ዩኒቨርስቲ የቴአትር አስተማሪ በሆኑት ዘላለም ተፈሪ ሲሆን በንጉሥ አባጅፋር ታሪክ ላይ ያተኩራል።

ቴአትሩ በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ሊበቃ የቻለው የኢትዮጵያ ቴአትር መቶኛ ዓመት መሙላቱን በማስመልከት መሆኑን ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ይቻላል።

የኢትዮጵያ ቴአትር መቶኛ ዓመት ፌስቲቫል ከነሐሴ 21 2013 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ነሐሴ 25 2013 ያበቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህንን የኢትዮጵያ ቴአትር መቶኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀውን የቴአትር ፌስቲቫል የቴአትር ባለሙያዎች ማሕበር እና የ ስለ ቴአትር ቡድን ጥምረት በጋራ ያዘጋጁት ነው።

በፌስቲቫሉ ላይ ከ40 በላይ አጫጭር እና የሙሉ ጊዜ ቴአትሮች እንዲሁም ከ450 በላይ ከያንያን በፌስቲቫል አቅርቦት ላይ ይሳተፋሉ ሲሉ አዘጋጆቹ አስታውቀው ነበር።

በዚህ አገር አቀፍ የቴአትር ፌስቲቫል ላይ የሚቀርቡ ተውኔቶች በአዲስ አበባ በሚገኙ ቴአትር እና ሲኒማ ቤቶች ላይ ይቀርባሉ።

ይህ ከነሐሴ 21 እስከ 25 2013 የሚቆየው ፌስቲቫል ላይ የሚቀርቡ ቴአትሮች በአጠቃላይ በነጻ ለህዝብ እንደሚቀርቡ አዘጋጆቹ ካሰራጩት መረጃ ላይ መረዳት ይቻላል።

የአባጅፋርን ታሪክ ለመድረክ ለማብቃት ያሰቡበትን ምክንያት መምህር ዘላለም ሲናገሩ "አባጅፋር በዲፕሎማሲ ይታወቃሉ። እንዲሁም አባ ጅፋር በሠላም እና በንግድ የታወቁ ነበሩ። የጅማን ታሪክና ባህል ምን እንደሚመስል ለማንፀባረቅ ስናስብ ከአባ ጅፋር የበለጠ በትክክል ሊገልፅልን የሚችል የለም በማለት የእርሳቸውን ታሪክ መረጥን" ብለዋል።

የቴአትሩ ደራሲ መምህር ዘላለም ቴአትሩን አባ ጅፋር ለመፎ ሲሉ ሰይመውታል። ይህም ወደ አማርኛ ሲመለሰ አባ ጅፋር ሁለተኛ እንደማለት ነው። መምህሩ ለቴአትሩ ለምን ይህን ስያሜ እንደሰጡ ሲያስረዱ "አባ ጅፋር ለመፎ ያልኩት አባ ጅፋር የጅማ ንጉሥ ስለነበሩ ነው፤ ታላቁ የጅማ ንጉሥ አንደኛ ሌላ አሉ" ይላሉ።

የቴአትሩ ደራሲ እና አዘጋጅ መምህር ዘላለም እንደሚናገሩት ከሆነ ቴአትሩ የአባ ጅፋርን ታሪክ፣ ሃሳብና ፍልስፍናዎችን ያካተተ ነው።

"ለምሳሌ አባ ጅፋር የሞት ፍርድን በሰዎች ላይ መፍረድን ይቃወሙ ነበር፤ እርሱን አሳይተናል። እንዲሁም በንግድ ሠላም እና ጦርነት ላይ ያላቸውን አቋም አንፀባርቀናል" ይላሉ የቴአትሩ ደራሱና አዘጋጅ መምህር ዘላለም።

አባ ጅፋር ለመፎ በመድረክ ላይ

ሠማኒያ ገፀባህሪያት እና የወደፊት እቅድ

አባ ጅፋር ቴአትር ላይ በጅማ ዩኒቨርስቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ተማሪዎች እና በጅማ ከተማ የአርት የወጣቶች ቡድን መሳተፋቸውን መምህር ዘላለም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ቴአትር አንድ ሰዓት ተኩል የሚፈጅ ሲሆን፣ ሰማንያ የሚሆኑ ገፀባህሪያት ተሳትፈውበታል።

"ይህ ቴአትር በኦሮምኛ እና በአማርኛ ነው የተዘጋጀው። ከባህልና ታሪክ ጋር የተያያዙትን በኦሮምኛ ነው ያዘጋጀነው። ንግግር ሆነው ታሪክ እና ባህልን የማያፋልሱትን ደግሞ በአማርኛ ቋንቋ ነው የሰራነው " ይላሉ።

ቴአትር በሁለት ቋንቋ የተመደረከበትን ምክንያት ሲገልፁም፤ ሁለቱንም ቋንቋ የሚያውቁ ሰዎች የኦሮሞ ባህልና ታሪክ እንዲማሩ ለማድረግ እና የቴአትሩ ገፀባህሪያትም በዩኒቨርስቲው የሚማሩ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በመሆናቸው ይህንኑ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆኑን መምህር ዘላለም ተናግረዋል።

የአባ ጅፋር ለመፎ ቴአትር እስካሁን ድረስ በጅማ ዩኒቨርስቲ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሞ ባህል ማዕከል ከክፍያ ነፃ ለተመልካቾች ቀርቧል።

ቴአትሩ እስካሁን ድረስ በጅማ ዩኒቨርስቲ እገዛ ለተመልካቾች የቀረበ መሆኑን አቶ ዘላለም ይናገራሉ።

ወደ ፊት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች በመዘዋወር ቴአትሩን ለተመልካቾች ለማቅረብ እቅድ እንዳላቸው አቶ ዘላለም ለቢቢሲ ተናግረዋል።