ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የስደተኞች ውዝግብን ተከትሎ ቤላሩስ ለአውሮፓ የሚደርሰውን ጋዝ እንደምታቋርጥ አስጠነቀቀች
በቤላሩስ ምዕራባዊ ድንበር ላይ እየተባባሰ ባለው የስደተኞች ቀውስ ምክንያት ማዕቀብ ከተጣለባት ለአውሮፓ የጋዝ አቅርቦትን እንደምታቋርጥ መሪዋ ዛቱ።
በአብዛኛዎቹ ከኢራቅ፣ ሶሪያ እና የመን የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤላሩስን ከፖላንድ በሚያዋስነው ድንበር ላይ ይገኛሉ። ወደ አውሮፓ ሕብረት አገራት የመሻገር ተስፋን የሰነቁት ስደተኞች በድንበሩ ላይ ከከባዱ ቀዝቃዜ ጋር እየታገሉ ናቸው።
የአውሮፓ ሕብረት ባለስልጣናት ቤላሩስ ቀውሱን በማባባስ የሕብረቱን ደህንነት ችግር ላይ እየጣለች ሲሉ ከሰዋል። ቤላሩስ ግን ክሱን ታስተባብላለች።
ይህን ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረት ቤላሩስ ላይ አዲስ ማዕቀብ ለመጣል ማቀዱ ተነግሯል።
ነገር ግን ሐሙስ ዕለት ሃገሪቱን ለረዥም ጊዜ ያስተዳደሩት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ "ተጨማሪ ማዕቀቦች ከተጣለብን… ምላሽ መስጠት አለብን" ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።
በቤላሩስን አቋርጦ ወደ አውሮፓ ሕብረት የሚገባውን የሩስያን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር በማስታወስ "አውሮፓን ብናሞቅም እነሱ ግን ያስፈራሩናል" ብለዋል።
በአውሮፓ የተፈጥሮ ጋዝ እጥረት እና የዋጋ ንረት እየተባባሰ በመጣበት ወቅት የመሪው አስተያየት አዲስ ፍራቻ ቀስቅሷል።
የኦክስፎርድ የኢነርጂ ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ካትጃ ያፊማቫ የሉካሼንኮ ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር መታየት አለበት ይላሉ።
"የአውሮፓ ሕብረት ቤላሩስን በጣም ከገፋ በጥንቃቄው መሠረት እርምጃ ሊወስድ ይችላል" ብለዋል ዶ/ር ያፊማቫ። ይህ ደግሞ ዩኬን ጨምሮ በመላው አውሮፓ የጋዝ ዋጋን ከፍ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ገልጸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ተጨማሪ ማዕቀቦች እስከ ሰኞ ሊጥል ይችላል። ሊወሰዱ ከሚችሉ እርምጃዎች መካከል ስደተኞችን የጫኑ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ቤላሩስ ዋና ከተማ ሚንስክ አየር ማረፊያ እንዳያርፉ ማገድን ይጨምራል።
የቱርክ አየር መንገድ በአንዳንድ የጉዞ መዳረሻዎቹ ላይ ለኢራቅ፣ ሶሪያ እና የመን ዜጎች የቲኬት ሽያጭን እንደሚገድብ አስታወቋል።
ኢራቅ ከቤላሩስ ለሚመለሱ ዜጎቿ በረራዎችን እያዘጋጀች መሆኑን ገልጻለች።
የአውሮፓ ሕብረት የሩሲያ መንግሥት አየር መንገድ የሆነው ኤሮፍሎት ስደተኞችን ወደ ቤላሩስ ያጓጉዛል በሚል ማዕቀብ ሊጣልበት እንደሆነም ተዘግቧል።
ቤላቪያ የተሰኘው የቤላሩስ ብሔራዊ አየር መንገድ በግንቦት ወር ከአውሮፓ ሕብረት ሰማይ ታግዶ ነበረ። የራያን አየር መንገድ በረራ ወደ ሚንስክ እንዲዞር ከተገደደ እና አንድ ተቃዋሚ ጋዜጠኛ ከታሰረ በኋላ ነው ይህ እገዳ የተጣለው።