አዛውንቶቹ መንትዮች በ107 ዓመታቸው በጊነስ መዝገብ ላይ ሰፈሩ

ኡሜኖ ሱሚያማ እና ኩሜ ኮዳማ

የፎቶው ባለመብት, GUINNESS WORLD RECORDS

የምስሉ መግለጫ, ኡሜኖ ሱሚያማ እና ኩሜ ኮዳማ
ታትሟል

ጊነስ የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ እድሜያቸው ከ107 ዓመታት እና ከ300 ቀናት የተሻገረውን ሁለት ጃፓናዊያን መንትኞች በሕይወት ያሉ አዛውንት መንትዮች ሲል መዘገበ።

ኡሜኖ ሱሚያማ እና ኩሜ ኮዳማ ከዚህ ቀደም ኪን ናሪታ እና ጂን ካኒ በተሰኙ ጃፓናዊያን ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ሰብረዋል። ኡሜኖ እና ኩሜን የሚያውቋቸው ሰዎች ተግባቢዎች እና ማኅበራዊ ሕይወትን የሚወዱ መሆናቸውን ይናገራሉ።

እአአ ጥቅምት 5 ቀን 1913 በሾዶሺማ ደሴት ነበር ወደዚህ ዓለም የመጡት።

ጊነስ ሁለቱን እህትማማቾች መመዝገቡን ይፋ ያደረገው ትናንት ሰኞ ሲሆን ይህም በጃፓን ብሔራዊ በዓል በሆነው የአዛውንቶች ቀን ላይ ነው።

በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት እህትማማቾቹ ወደሚኖሩበት የተለያየ የጃፓን ክፍል የምዝገባው የምስክር ወረቀት እንዲላክ መደረጉም ታውቋል።

መንትዮቹ እአአ ከመስከረም 1 ቀን 2021 ጀምሮ የክብረ ወሰኑ ባለቤት በመሆናቸው እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የድንቃ ድንቅ መዝገቡ ጊነስ ሰኞ በሰጠው መግለጫ የቀድሞው የክብረ ወሰኑ ባለቤቶች ኪን እና ጂን ለ107 ዓመታት እና 175 ቀናት ክብረ ወሰኑን ይዘው ቢቆዩም ኪን እአአ ጥር 2000 ሕይወታቸው አለፈ። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ጂን አልፈዋል።

ጂን እና ኪን እአአ ነሐሴ 1 ቀን 1892 የተወለዱ ሲሆን፤ የስማቸው ትርጉምም ወርቅ እና ብር የሚል ፍቺ ነበረው።

ከህልፈታቸው አስር ዓመታት ቀደም ብሎ ታሪካቸው በመገናኛ ብዙኃን ተደጋግሞ የሚነገር ዝነኞች ሆነውም ነበር።

አዲሶቹ ባለ ክብረወሰን መንትዮች ኡሜኖ እና ኩሜ ስለደረሱበት እድሜ አስቂኝ ቀልዶችን እንደቀለዱም ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።

ኡሜኖ የአራት ልጆች እናት ሲሆኑ ኩሜ ሦስት ልጆች አሏቸው።

ጃፓን ውስጥ ሰዎች ረዥም ዓመታት ይኖራሉ። አዛውንቶችም ከፍተኛ ክብር ይሰጣቸዋል።

እስካሁን በጃፓን የተመዘገበው ትልቁ እድሜ 118 ዓመት ሲሆን የዚህ ክብረ ወሰን ባለቤትም ጃፓናዊቷ ካኔ ታናካ ናቸው።