ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የአሜሪካ የንግድ ተቋማት ሠራተኞች ካልተከተቡ በየሳምንቱ እንደሚመረመሩ ተነገራቸው
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በትልልቅ የንግድ ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞች የኮሮናቫይረስ ክትባት የማይወስዱ ከሆነ በየሳምንቱ ምርመራ እንደሚደረግላቸው ተናገሩ።
ፕሬዘዳንቱ አዲስ የኮሮናቫይረስ መከላከያ እርምጃዎችን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የፌደራል መንግሥቱ ሠራተኞች እንዲከተቡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
በአገሪቱ ከ650,000 በላይ አሜሪካውያን በቫይረሱ ሞተዋል። ሆስፒታሎችም እየተጨናነቁ ነው።
ወረርሽኙ በቅርቡ ጋብ እንደሚል ባይደን ተናግረው የነበረ ቢሆንም ዴልታ የተባለው የቫይረሱ አይነት ነገሮችን ለዋውጧል።
የሠራተኞች ሚንስትር ከ100 በላይ ተቀጣሪዎች ያሏቸው የግል የንግድ ተቋማት ተቀጣሪዎቻቸውን እንዲያስከትቡ እንዲጠይቅ በባይደን ታዟል። ሰራተኞች ካልተከተቡ ግን በየሳምቱ ከቫይረሱ ነጻ የሚል ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።
ይህ ውሳኔ አሜሪካ ውስጥ ወደ 80 ሚሊዮን የሚጠጉ ሠራተኞችን ይመለከታል።
"የነጻነት ወይም የግል ምርጫ ጉዳይ አይደለም። ውሳኔ የተላለፈው ራሳችሁን እና በአካባቢያችሁ ያሉትንም ከበሽታ እንድትጠብቁ ነው" ብለዋል ፕሬዘዳንቱ።
ውሳኔው 17 ሚሊዮን የጤና አገልግሎት ሰጪዎችን እንደሚያካትት ተናግረዋል።
ብዙ አሜሪካውያን ቢያንስ አንድ ዙር ክትባት ቢወስዱም፤ ባይደን ግን ቫይረሱን መቆጣጠር ያልተቻለው 25% በሚደርሱት ያልተከተቡ ዜጎች ምክንያት ነው ብለዋል።
አንዳንድ ፖለቲከኞች ቫይረሱን ለመግታት የሚደረገውን ትግል እያሰናከሉ እንደሆነም አክለዋል።
የንግድ ተቋማት ሠራተኞች ከሥራቸው እና ከክትባቱ እንዲመርጡ የሚያስገድደው አዲስ መርህ ውዝግብ እንደሚያስነሳ ይጠበቃል።
አንዳንድ ተቀጣሪዎች ክትባት ለመከተብ በሚሄዱበት ቀን ወይም ከክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳት ለማገገም በሚወስዷቸው ቀናት ከሥራ እረፍት እንደማያገኙ ሲናገሩ ነበር።
ባይደን በበኩላቸው፤ ሠራተኞቻቸው ክትባት እንዲወስዱ የማያመቻቹ ተቋማት በሺዎች የሚቆጠር የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልባቸው አሳስበዋል።
2.5 ሚሊዮን የሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ክትባት ለመውሰድ ካልፈቀዱ ከሥራ እንደሚባረሩ ፕሬዘዳንቱ ጠቁመዋል።
ባይደን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ካወጧቸው መርሆች መካከል፤ አውሮፕላን ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የማያደርጉ ሰዎችን በገንዘብ መቅጣት ይገኝበታል።
ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎት ሰጪዎች እንደሚላኩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሰዎች ቤታቸው ሆነው የሚመረመሩበት መሣሪያ በብዛት እንዲሰራጭ ይደረጋል ተብሏል።
የአሜሪካ የበሽታ መከላከያ እና ቁጥጥር ተቋም እንደሚለው፤ 64% አሜሪካውያን ሙሉ ለሙሉ ሲከተቡ፤ 75% ያህሉ አንድ ዙር ጠብታ ወስደዋል።