ከአፍጋኒስታን የሚወጡ የመጀመሪያዎቹ አስተርጓሚዎችና ቤተሰቦቻቸው በቅርቡ አሜሪካ ይደርሳሉ

አስተርጓሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ከአፍጋኒስታን የሚወጡ 2500 የሚደርሱ የመጀመሪያዎቹ አስተርጓሚዎች እና ቤተሰቦቻቸው ሐሙስ አሜሪካ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ልዩ የስደተኞችን ቪዛ (ኤስቪአይ) ሒደታቸውን እስኪያጠናቅቁ በዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ በሚገኘው ፎርት ሊ የጦር ሰፈር ይቆያሉ፡፡

ልዩ የስደተኞችን ቪዛ ፕሮግራም እአአ በ2001 በተጀመረው የአፍጋኒስታን ጦርነት ከአሜሪካ መንግሥት ወይም በአሜሪካ ከሚመራው ወታደራዊ ኃይል ጋር ለሠሩ ይሰጣል፡፡

የታሊባን መስፋፋትን ተከትሎ አሜሪካንን በረዱ አፍጋኒስታናዊያን ላይ የሚደርሰው ዛቻ ከፍ ብሏል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ 2,500 አፍጋኒስታናዊያንን የማጣራት ሒደቱ፣ የሕክምና ምርመራ እና ሌሎች ለቪዛ የሚያስፈልጉ ነገሮችን እስኪያጠናቅቁ በፎርት ሊ ይቆያሉ፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አፍጋኒስታናውያኑን የያዘው አውሮፕላን መድረሱን በስህተት ለቢቢሲ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፡፡

እአአ ከ2008 ጀምሮ ወደ 70,000 የሚጠጉ ልዩ የስደተኞችን ቪዛ ያገኙ አፍጋኒስታናዊያን በአገሪቱ እንዲሰፍሩ መደረጉን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት አንድ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን እንዳሉት፤ ልዩ የስደተኞችን ቪዛ አመልካቾች ቁጥር ከ20 ሺህ በላይ ነው። ግማሽ ያህሉ የሂደቱን የመጀመሪያ ደረጃ ገና አላጠናቀቁም፡፡

በአፍጋኒስታን ተሰማርተው የነበሩት የቀድሞው የአሜሪካ ጦር አዛዥ ማይክ ጄሰን ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ በታሊባን ቁጥጥር ሥር ባሉ አካባቢዎች ለልዩ የስደተኞችን ቪዛ የሚያስፈልገውን ሰነድ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አስተርጓሚዎችን "የመሞት አደጋ" ውስጥ ይወድቃሉ፡፡

"ይህ በመሠረቱ ለአሜሪካ የሚሠሩ አስተርጓሚ ስለመሆንዎ ሙሉ በሙሉ ማመን ነው። ስለዚህ በማስረጃው እንዲጓዙ እየጠየቅን ነው" ብለዋል፡፡

ለትርፍ ያልተቋቋመው ኖ ዋን ሌፍት ቢሃይንድ በትንሹ 300 የአሜሪካ አጋሮች የሆኑ አፍጋኒስታናዊያን ወይም የቤተሰብ አባላቸው መገደላቸውን ገምቷል፡፡

ታሊባን በአሜሪካ መራሹ ወረራ በ2001 ከሥልጣን ተወግዷል፡፡

ዓለም አቀፍ ወታደሮች ከአገሪቱ መውጣታቸውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት በአማጺው ታሊባን እና በአፍጋኒስታን መንግሥት ወታደሮች መካከል የተደረገው ውጊያ ጨምሯል፡፡

ታሊባን በቅርቡ ተዋጊዎቹ 85 በመቶ የአገሪቱን ክፍልን መቆጣጠሩን ቢገልጽም መንግሥት አጣጥሎታል። ይህን አኃዝ በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡