በትራምፕ እንዲተገበር ተደርጎ የነበረው የሞት ቅጣት እንዲቆም ተደረገ

የአሜሪካ ማረሚያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከ 17 ዓመታት በኋላ በትራምፕ አስተዳደር በ 2020 እንደገና የተጀመረው የፌዴራል ሞት ቅጣት እንዲቆም አዘዘ።

የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ሜሪክ ጋርላንድም በሞት ቅጣት ዙሪያ ያሉ ህጎች እንዲታዩ አዘዋል።

ውሳኔው የፕሬዚደንት ጆ ባይደን ድጋፍ ያለው ሲሆን ጋርላንድን የሾሙትም የሞት ቅጣቶችን ለማስቆም ነበር።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት የመጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው ወራት 13 የፌደራል የሞት ፍርዶች ተፈፅጽመዋል።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ጋራላንድ የውሳኔው ማቋረጥን ሲገልጹ የሞት ቅጣት የተፈረደባቸውን አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ማህበረሰቦችን ጉዳይ አንስተዋል።

"የፍትህ መምሪያ በፌዴራል የወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው በአሜሪካ ህገ-መንግስት እና ህጎች የተረጋገጡ መብቶችን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊ እና ሰብአዊ ሆኖ መታየቱን ማረጋገጥ አለበት" ብለዋል።

ባይደን ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ በፌደራል ደረጃ ጥፋተኛ ተብሎ በሞት የተቀጣ የለም። እንደ የሞት ቅጣት መረጃ ማዕከል ከሆነ በአሁኑ ወቅት በፌዴራል የሞት ቅጣት ፍርደኞች 50 ያህል ይሆናሉ።

የፈፌደራል ሞት ፍርድ እንዲተገበር እአአ በ 2020 ትዕዛዝ የሰጡት የቀድሞው ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ዊሊያም ባር ናቸው። የፌደራል መንግስቱ የቆመው "ተጎጂዎቹ እና ቤተሰቦቻቸው የፍትህ ስርዓታችን ያስተላለፈውን ቅጣት እንዲያገኙ ነው" ብለዋል።

ጋርላንድ በተጨማሪም እስረኞች በሚሞቱበት ጊዜ ከባድ ህመም አጋጥሟቸው ሊሆን እንደሚችል የሚገልጹ ዘገባዎች በመኖራቸው ገዳይ መርፌ በሚሰጥበት ወቅት የሚሰጡትን መድኃኒቶች እንዲገመግሙ ለባለስልጣናት አዘዋል።

አብዛኛው የአሜሪካ የሞት ፍርድ የሚፈጸመው በግዛቶች ደረጃ ሲሆን ወደ 2500 የሚሆኑ እስረኞች የሞት ፍርደኞች ናቸው። ቴክሳስ ከ 1976 ጀምሮ በ 570 የሞት ቅጣቶችን በመፈጸም በሃገሪቱ ቀዳሚዋ ግዛት ናት።

ባይደን ለፕሬዝዳንትነት በሚወዳደሩበት ወቅት የፌዴራል የሞት ፍርዶችን ለማስቆም ቃል ሲገቡ ግዛቶችም ተመሳሳይ እርመጃ እንዲወስዱ እንደሚያበረታቱ አስታውቀው ነበር። ከወዲሁም ወደ ግማሽ የሚሆኑት ግዛቶች የሞት ቅጣትን ሰርዘዋል።

እአአ በመጋቢት 2021 ቨርጂኒያ የሞት ቅጣትን ያስቀረች የመጀመሪያዋ የደቡብ ግዛት ሆናለች፡፡