ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"መንገድ ላይ ታፍነው የቀሩ ተማሪዎች አሉ" ከራያ ዩኒቨርሲቲ ማይጨው ግቢ የወጡ ተማሪዎች
የፌደራል መንግሥት በትግራይ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁንና ጦሩን ማስወጣቱን ተከትሎ ከራያ ዩኒቨርሲቲ ማይጨው ግቢን በስጋት ለቀው የወጡ ተማሪዎች መንገድ ላይ 'ታፍነው የቀሩ ተማሪዎች' መኖራቸው ተናገሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸውና በወልዲያ የሚገኙ ተማሪዎች በመከላከያ ጥበቃ ሲደረግላቸው እንደነበር ገልጸው፤ ጦሩ ሲወጣ ባደረባቸው ስጋት በሌሊት ግቢውን ለቀን ወጥተናል ብለዋል።
በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ልጆቻቸውን የላኩ ወላጆች መንግሥት ልጆቻቸውን እንዲያስወጣላቸውና ስለ ደኅንነታቸው ግልጽ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
ቢቢሲ በትግራይ የኢንተርኔትና የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ዝግ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን ሁኔታ ማጣራት አልቻለም።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ግን ተማሪዎቹን በተመለከተ ትናንት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው መልዕክት ከተለያዩ አካላት፣ ዩኒቨርሲቲዎቹ አመራሮች እና ከዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ በመጥቀስ ተማሪዎቹ በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብሏል።
ተማሪዎቹ የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ያሉ እንዳሉም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የፌደራል መንግሥት ጦር መቀለን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች የክልሉን መዲና የተቆጣጠሩት ከሦስት ቀናት በፊት ሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ነበር።
በራያ ዩኒቨርሲቲ ማይጨው ካምፓስ የሦስተኛ ዓመት የሥነ ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ተማሪ የሆነችው ስንዱ ገበያው ባለፈው ሰኞ ሌሊት ስድስት ሰዓት ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በመሆን ግቢውን ለቃ እንደወጣች ለቢቢሲ ገልጻለች።
"ከዚህ ቀደም መከላከያን ጥላ አድርገን ነበር የምንማረው፤ መከላከያ ሙሉ በመሉ ሲወጣ ለሕይወታችን በመስጋት ነው የወጣነው፤ እቃችንን እንኳን አልያዝንም" ብላለች።
ከ200 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችም ሌሊቱን በእግራቸው ሲጓዙ አድረው መሆኒ ከተማ ንጋት 11 ሰዓት ላይ መግባታቸውን ትገልጻለች።
እርሷ እንደምትለው ማይጨው ከመሆኒ 20 ኪ.ሜ. ይርቃል።
"በእግራችን እየተጓዝን መከላከያዎችን ደረስንባቸው፤ ከዚያ አላማጣ ገባን። ከአላማጣ ቆቦ አሳፈሩን፤ ከቆቦ ወልዲያ ገባን" በማለት የተጓዙበትን መስመር ገልጻለች።
ስንዱ እነርሱ በእግራቸው ሲጓዙ መንገድ ላይ የገጠማቸው ነገር ባይኖርም "ውሃ ለመጠጣት ወደኋላ ከቀሩት ውስጥ 5ቱ ተማሪዎች እስካሁን የት እንዳሉ አይታወቅም" ስትል ተናግራለች።
ስንዱን ቢቢሲ ባነጋገራት ወቅት የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከቆቦ የተቀበላቸውን ተማሪዎች ወደ መጡበት አካባቢ እየሸኘ ነበር።
ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የቀሩ ጓደኞቻቸው የሚወጡበት ሁኔታ እንዲመቻችና መንገድ ላይ የቀሩትን ተማሪዎች ሁኔታ እንዲጣራ መንግሥትን ጠይቀዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይፍሩ ዘሪሁን ከራያ ዩኒቨርሲቲ ማይጨው ግቢ የወጡ 220 ተማሪዎችን ወደ መጡበት አካባቢ እየሸኙ እንደሆነ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አቶ ይፍሩ እንዳሉት በስጋት ግቢውን ለቀው የወጡትን ተማሪዎች ከትናንት በስቲያ (ረቡዕ ዕለት) ጀምሮ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ነበር የቆዩት።
"ከቆቦ ተማሪዎቹን የተቀበለው ዩኒቨርስቲ ወጪያቸውን ችሎ መኪና በማዘጋጀት ወደ መጡበት አካባቢ እየሸኘ ነው" ብለዋል ኃላፊው።
በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ የየተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ በርካታ ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን፤ የፌደራል መንግሥቱ የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱ ከክልሉ ሲወጣ የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የተማሪዎቹ ቤተሰቦች ስጋት ላይ ወድቀዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ተማሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት ጥቅምት 24/ 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝን ማጥቃቱን ተከትሎ ላለፉት ስምንት ወራት በክልሉ ጦርነት ሲካሄድ ቆይቷል።
በጦርነቱ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ለረሃብ አፋፍ ላይ ሲገኙ ከአምስት ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ አስቸኳይ ምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ ብሏል።