የሕፃን ሰውነት በአሲድ ያሟሟው 'ማፊያ' ከእስር መፈታቱ ቁጣ አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሲሲሊው የወንጀል ቡድን (ማፊያ) አለቃ ጆቫኒ ብሩስካ ከእስር መፈታቱ በርካቶችን አስቆጣ።
ጆቫኒ ከተከሰሰባቸው ወንጀሎች መካከል የሕፃን ሰውነትን በአሲድ ማሟሟት ይገኝበታል።
'ፒፕል ስሌየር' ወይም ሰው በላው በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ጆቫኒ፤ ከ100 በላይ ግድያዎች ውስጥ እጁ እንዳለበት አምኗል። ይህም ታዋቂው የጸረ ማፊያ ዓቃቤ ሕግ ጆቫኒ ፋልኮን መግደልን ይጨምራል።
ጆቫኒ የወንጀል ጓዶቹን በመጠቆም ዓቃቤ ሕግን ተባብሯል። ከ25 ዓመታት እስር በኋላ መፈታቱ ጉዳት ያደረሰባቸው ሰዎችን ወዳጅ ዘመዶች አስቆጥቷል።
ጆቫኒ ብሩስካ ማነው?
የ64 ዓመቱ ጆቫኒ፤ ኮስታ ኖስትራ የተባለ የሲሲሊ የወንጀል ቡድን አባል ውስጥ ቁልፍ ሰው ነበር።
እአአ በ1992 የወንጀል ቡድኖችን ጉዳይ በመመርመር የሚታወቀው ዳኛ ጆቫኒ ፋልኮን የተገደለበትን ቦንብ አፈንድቷል። በፍንዳታው የዳኛው ባለቤትና ሦስት ጠባቂዎቹም ተገድለዋል።
ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ የዳኛው ባልደረባ የሆነው ፓውሎ ብሮሴሊኖ ተገድሏል።
እነዚህ ግድያዎች መላው ጣልያንን ያስደነገጡና ወንጀለኛ ቡድኖችን በተመለከተ ጥብቅ ሕግ እንዲወጣ ያደረጉም ናቸው።
ጆቫኒ ፈጽሜያቸዋለሁ ካላቸው ግድያዎች እጅግ አሰቃቂው የ11 ዓመት ታዳጊ ነው። ጁሴፒ ዲ ማቶ የተባለው ታዳጊ የሌላ ወንጀል ቡድን አባል ልጅ ነበር።
ጆቫኒ ልጁን ለመግደል የወሰነው አባቱ ከድቶኛል ብሎ ነው። ልጁን አሳግቶ ካሰቃየው በኋላ አንቆት ሰውነቱን አሲድ ውስጥ አሟምቶታል።
የታዳጊው ቤተሰቦች ልጃቸውን መቅበር አልቻሉም ነበር።
ጆቫኒ እአአ በ1996 ከታሰረ በኋላ የእስር ጊዜውን ለመቀነስ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆኗል።
ከ1980 እስከ 1990 ድረስ በወንጀል ቡድኖች ከተፈጸሙ ወንጀሎች ጀርባ ያሉ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ እገዛ አድርጓል።
ከእስር ሲለቀቅ ምን ተባለ?
ጆቫኒ መፈታቱ ጉዳት ያደረሰባቸው ሰዎችን ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች አስቆጥቷል።
በጆቫኒ ከተገደሉ ጠባቂዎች የአንዱ ባለቤት ቲና ሞንትሪዎ፤ ለሪፐብሊካ ጋዜጣ "መፈታቱ ፍትሐዊ አይደለም። አበሳጭቶኛል" ብላለች።
"ከ29 ዓመታት በኋላም ጆቫኒ ስለፈጸመው ግድያ አናውቅም። መንግሥት ከኛ ጎን አልቆመም። ቤተሰቤን ያመሰቃቀለው ሰው ነጻ ወጥቷል" ስትልም አክላለች።
የተገደለው ዳኛ እህት ማርያ ፋልኮን ጆቫኒ ከእስር በመለቀቁ ማዘኗን ገልጻለች።
በርካታ የጣልያን ፖለቲከኞች ጆቫኒ ከእስር መለቀቁን ኮንነዋል።
የቀኝ ዘመሙ ሊግ ፓርቲ መሪ ማቶ ሳልቪኒ "የወንጀል ቡድን አለቃው ጆቫኒ ከ25 ዓመት በኋላ ከእስር ተለቋል። ይህ ለጣልያናውያን አይገባም" ብለዋል።
የዴሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ኤንሪኮ ሌታ ደግሞ "ሆድን በቡጢ የመታት ያህል ትንፋሽ የሚያሳጥር ውሳኔ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።












