እስራኤል፡ እስካሁን 100 ሰዎችን ያቆሰለው ተቃውሞ ዛሬም በእየሩሳሌም ሊቀጥል ይችላል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለሶስተኛ ተከታታይ ቀናት በእየሩሳሌም የሚኖሩ ፍልስጤማዊያን የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን ዛሬም ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።
የዛሬው ሰልፍ የአይሁዶች በጠሩት ሰልፍ ምክንያት የሃይል እርምጃዎች ይታዩበታል የሚሉ ስጋቶች እያየሉ ነው።
ዛሬ የሚከበረው ዓመታዊው የእየሩሳሌም የባንዲራ ቀን ሲደርስ ባንዲራ የያዙ ወጣቶች በሙስሊም አካባቢዎች ያልፋሉ። ይህም የሚካሄደው እስራኤል ምስራቅ እየሩሳሌምን የያዘችበትን ቀን ለመዘከር ነው። በርካታ ፍልስጤማዊያን ይህንን ድርጊት ትንኮሳ ነው ይሉታል።
አሞጽ ጊላድ የተባሉ አንድ የቀድሞ የእስራኤል ከፍተኛ የጦር መኮንን የዚህ ዓመቱ ትዕይነተ ሕዝብ እንዲሰረዝ ወይም እንዲራዘም በወታደራዊው የራዲዮ ጣቢያ ላይ ጠይቀዋል። ይህ ውጥረት ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን አሰምተዋል።
ለውጥረቱ መነሻ የሆነውም በምስራቅ እየሩሳሌም በሚገኘው የሼክ ጃራ ክፍል የፍልስጤማዊያን ቤተሰቦችን የማፈናቀል አደጋ መጋረጡ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን ሰልፈኞች ብሎም ከ 20 በላይ የእስራኤል ፖሊሰች ባለፈው ሶስት ቀናት በነበሩ ግጭቶች ተጎድተዋል።
እሁድ ምሽት ፍልስጤማዊያን ሰልፈኞች በእስራኤል ፖሊስ ላይ ድንጋይ ወርውረዋል። ፖሊስ በአፀፋው ስልፈኞችን ለመበተን ሙከራ አድርጓል።
በጥንታዊቷ የደማስቆ ከተማ መግቢያ ላይም ጠንከር ያለ ግጭት መታየቱም ተዘግቧል።
ተመሳሳይ ፍጥጫ እና ግጭቶች በሰሜናዊ እስራኤል ሃፋ ከተማም ታይቷል። እንዲሁም የዌስት ባንኳ ራማላህም በፍልስጤማዊያን ብሎም በፖሊስ መካከል የነበረውን ፍጥጫ ካስተናገዱ ከተሞች መካከል ነች።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከፍልስጤማዊያን በተቀራኒ በመቆም የፖሊስን ድርጊት የሚደግፍ መግለጫ ሰጥተዋል።
መንግሥታቸውም "ማንኛውንም አይነት የከተማዋን ሰላም የሚገዳደር የአክራሪነት ተግባርን" መፍቀድ እንደሌለበትም ተናግረዋል።












