የአፍሪካ ሃገራት በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከምዕራባዊያን በተለየ ለምን ለቻይና ያደላሉ?

ታትሟል

ቻይና በሰሜን ምዕራባዊ ክፍል የሚገኙ የኡጉር ሙስሊሞችን እያሰቃየች ነው በሚል በርካታ አገራት ጫና ለማሳደር እየሞከሩ ቢሆንም የአፍሪካ አገራት ግን እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።

እንደውም አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ዲፕሎማቶች በቅርቡ በቤዢንግ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተካፍለው ቻይና በተጠቀሰው ግዛት የምትወስደውን እርምጃ እንደሚደግፉ ገልጸው ነበር።

ቢያንስ አንድ ሚሊዑን የሚሆኑ የኡጉር ሙስሊሞች ዢንግጃንግ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ካምፖች ውስጥ ታጉረው እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር።

"የዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ" በሚል ሽፋን ለዓመታት የቆየው ይህ ካምፕ አስተሳሰብን የሚያጥብ፣ ጉልበትን የሚያዝል፣ እምነትን የሚሸረሽር፣ ኅቡዕ የግዞት ማዕከል ነው ተብሏል።

ቢቢሲ የተለያዩ ይፋዊ መረጃዎችን በማሰባሰብና በአስርታት ለሚቆጠሩ የቤተሰብ አባላት ቃለ መጠይቅ አድርጎ ባገኘው መረጃ መሠረት በአንድ ከተማ ውስጥ ከ400 በላይ የሚሆኑ ሕፃናት አብዛኛዎቹ እናትና አባቶቻቸው በማረሚያ ቤት አልያም በማቆያ ማዕከላት ውስጥ የሚገኙ ናቸው።

ዢንጂያንግ ባለው ከፍተኛ የቁጥጥር ስራ ምክንያት የውጭ ሃገር ጋዜጠኞች በቀን 24 ሰአት ክትትል የሚደረግባቸው ሲሆን በአካባቢው የሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበል እጅግ ከባድ ነው። ነገር ግን ቱርክ ውስጥ ነዋሪነታቸውን ያደረጉና ታሪካቸውን ለማጋራት ፈቃደኛ የሆኑ ብዙ ቻይናውያን ይገኛሉ።

በቱርክ ዋና ከተማ ኢስታንቡል በስደት የሚገኙት አብዛናዎቹ ልጆቻቸውን ጨምሮ በርካታ የቤተሰብ አባላቶቻቸው የት እንደሚገኙ የማያውቁ ሲሆን የበፊት ምስሎቻቸው ብቻ እንደ ማስታወሻ እጃቸው ላይ እንደቀረ ይናገራሉ።

ቻይና በበኩሏ "የአክራሪ ሙስሊሞች ሞገደኛ አስተሳሰብ የምገራበት ከፍተኛ የትምህርትና ሥልጠና ተቋሜ ነው" ትላለች።

"አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት በዢንጂያንግ ወንጀል እየተፈጸመ ነው በማለት የራሳቸውን አጀንዳ ለማሳካት እየጣሩ ነው'' ሲሉ ተደምጠዋል የቡርኪና ፋሶው አምባሳደር አዳማ ኮምፓዎሬ። አምባሳደሩ ይህን ያሉት ቻይና የዢንጂያንግ ክልል በአፍሪካውያን አምባሰደሮች አይን በሚል ባዘጋጀችው ውይይት ነው።

ሱዳንና እና ኮንጎ ብራዛቪልም በዝግጅቱ የተሳተፉ ሲሆን የኮንጎ ብራዛቪሉ ተወካይ ዳንኤል ኦዋሳ በክልሉ ቻይና ሽብረተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች ደግሞ ይህን መሰል ስብሰባዎች አፍሪካ ከቻይና ጋር በተያያዘ ለሚከተሉት ዝም የማለት ፖሊሲ ማሳያ ነው ብሏል ባወጣው መግለጫ።

'' ምናልባት የተለመደ አይነት የዲፕሎማሲ ስራ ሊመስል ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን የአፍሪካ መንግስታት ቻይና በኡጉር ሙስሊሞች ላይ የምትወስደውን እርምጃ በዝምታ ማለፋቸው መዘዝ አለው'' ይላሉ የድርጅቱ የአፍሪካ አድቮኬሲ ዳይሬክተር የሆኑት ካሪን ካኔዛ ናንቱልያ።

ነገር ግን ብራሰልስ በሚገኘው የዓለማቀፍ አስተዳደር ተመራማሪ የሆነችው ኤጄቪዮሜ ኦቶቦ እንደምትለው በርካታ የአፍሪካ መሪዎች በሶስት ወነኛ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው። እነዚህ የሰብአዊ መብት፣ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትና የሌሎች ውስጥ ጉዳዮች ላይ አለመግባት ናቸው።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አፍሪካ ከቻይና ጋር የጀመረችው ጠበቅ ያለ ግንኙነት ከተቀረው ዓለም በተለይ ደግሞ ከምዕራባውያኑ እንድተርቅ እያደረጋት ነው የሚሉ አልጠፉም።

ባሳለፍነው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ካውንስል ጄኔቫ ላይ ከአወዛጋቢዋ ሆንግ ኮንግ ጋር በተያያዘ ባደረገው ስብሰባ ላይ 25 የአፍሪካ አገራት በጉዳዩ ላይ ከቻይና ጎን እንደሚቆሙ ገልጸው ነበር።

ከወራት በኋላ ደግሞ ቻይና በዢንጂያንግ፣ ሆንግ ኮንግ እና ቲቤት ትፈጽመዋለች በተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት ተግባሩን ለማውገዝ በተደረገው ጥረት ላይ አንድም የአፍሪካ አገር አልተሳተፈም ነበር። እንደውም በተዘጋጀው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ማናቸውም አልፈረሙም።

ሂዩማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ መሪዎች ከዐለማቀፋው አሳሳቢ ጉዳዮች ይልቅ ከቻይና የሚያገኙትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያስቀደሙ ሲል ይከሳል።

የቻይና አፍሪካ መስራቾች መካከል አንዱ የሆኑት ኤሪክ ኦላንደር ደግሞ የአፍሪካ መሪዎች ቻይናን ላለማበሳጨት መሞከራቸው ቅድሚያ የሚሰጡት ፖሊሲ መሆኑ ሊገባን ይገባል ይላል።

'' አፍሪካውያንን እንዲህ ብለው የሚተቹ ሰዎች የማይረዱት ነገር ደሀና በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ከቻይና በርካታ ብድሮችን የወሰዱ ናቸው። በተጨማሪም አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴያቸው ከቻይና ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ከቻይና ጋር በመሰል ጉዳዮች ተጣልቶ ያላቸውን ማበላሸት አይፈልጉም። ይህ ማንም አገር የሚከተለው ፖሊሲ ነው'' ይላል።

ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካና በቻይና መከካል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ትርጉም የሚሰጠው በአውሮፓውያኑ 1970 ላይ ቻይና የተባቡት መንግስታትን እንድትቀላቀል የአፍሪካ አገራት የተጫወቱት ሚና ነው። በወቅቱ አሜሪካ ቻይና አባል እንዳትሆን ከፍተኛ ጫና ስታሳድር ነበር።

''ከዛ ጊዜ በኋላ በሁለቱ መከካል ያለው ግንኘዑነት በጣም እየጠነከረ መጥቷል'' ይላል መቀመጫውን ኬንያ ያደረገ የቻይና አፍሪካ ተንታኙ ክሊፍ ምቦያ።

'' ላለፉት 30 ዓመታት ያክል ቻይና በየዓመቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ አፍሪካ ትልካለች። ይህ ደግሞ የሚያሳየው ቻይና ቀጣይነት ያለው ግንኙነት ከአፍሪካ ጋር መመስረት እንደምትፈልግ ማሳያ ነው። አፍሪካውያን ደግሞ ይህንን እንደ ትልቅ አጋጣሚ ነው የሚመለከቱት''

በርካታ ወጣት አፍሪካውያን በዚህ ሀሳብ ብዙም ደስተኞች አይደሉም። ምክንያቱ ደግሞ በአሜሪካ የሚመራውን ኢኮኖሚያዊ ሞዴል እያዩ ነው ያደጉት። በበርካታ ነገሮችም አሜሪካን ተመራጭ ሲያደርጉ ይታያል ይላል በቅርቡ የተሰራ አንድ ጥናት።

ነገር ግን አዋቂ አፍሪካውያን እና መሪዎች ጉዳዩን በተለየ መልኩ ነው የሚመለከቱት። ለዚህም ላለፉት ቢያንስ 20 ዓመታት የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን እና ኢኮኖሚያቸውን ለማጠናከር ፊታቸውን ወደ ቻይና ያዞሩት።

የቻይና እና አፍሪካን ግንኙነት በደንብ ለመረዳት ቻይና የጀመረችውን ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ማየት በቂ ነው። በቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላሮችን የሚያንቀሳቅሰው ይህ ፕሮጀክት በ46 የአፍሪካ አገራት ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ሁሉም ተስማምተው ፈርመውበታል።

''ይህን መሰል ፕሮጀክት መቼ ነው ምዕራባውያኑ ያቀረቡት? በዚህ ደረጃ ሌሎች አገራት ይህንን ሲኣደርጉ አልተመለከትንም'' ይላል ክሊፍ ምቦያ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ቻይና ለትልልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች የምታቀርበው ብድርና መክፈል ለማይችሉት ደግሞ በጋራ ለማልማት የምታቀርበውን ሀሳብ በጥርጣሬ ይመለከቱታል። ለዚህ በዋነኛነት የሚጠቀሰው የኬንያው የባቡመር መስመር ዝርጋተ ነው። በርካቶችም ቻይና ፕሮጀክቱን ጠቅልላ ልትወስደው ነው የሚል ሀሳብ ያቀርቡ ነበር።

የክትባት ዲፕሎማሲ

የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ከተከሰተ ወዲህ ቻይና ለበርካታ የአፍሪካ አገራት የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ ነበር። የአፍና እፍንጫ መሸፈኛዎችን ጨምሮ ሌሎች የመከላከያ ቁሳቁሶችን ስትልክ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ቻይና የክትባት ዲፕሎማሲ በሚል የጀመረችው እንቅስቃሴ 13 የአፍሪካ አገራትን የደረሰ ሲሆን አገራቱ ክትባቱን ገዝተዋል አልያም በድጋፍ መልክ አግኝተውታል።

በሌለ በኩል ምዕራባውያኑ በተለይ ደግሞ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱን ለድሀ አገራት ለማዳረስ የሰሩት እዚህ ግባ የሚባል ስራ የለም። ምናልባት ዓለማቀፍ የክትባት ጥምረት በሆነው ኮቫክስ በኩል ድጋፍ አድርገዋል ሊባል ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን በዚህ ጥብረት ውስጥ ቻይናም አለችበት።

ኮቫክስ እስካሁን ድረስ 18 ሚሊየን ክትባቶችን ለ41 የአፍሪካ አገራት አከፋፍሏል።

ለኮቪድ-19 የሚሆን ክትባትን በመጠቀም በዓለም ላይ ያላቸውን ተጽህኖ ለማሳየት እየሞከሩ ያሉ አገራት ሲኖሩ በአሁኑ ሰአት ትልልቅ አገራት የክትባት ግብግብ ላይ ናቸው።

ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የዩኬው የውጭ ጉዳይ ጸሀፊ ዶሚኒክ ራብ በማደግ ላይ ያሉ አገራት ከቻይና እና ሩሲኣ የሚመጡ ክትባቶችን እንዳይጠቀሙና የተሻለ ክትባት እስኪመጣላቸው እንዲጠብቂ ተናግረው ነበር።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሰክረተሪ አንቶኒ ብሊንከን ደግሞ በቅርቡ ከአፍሪካ ከመጡ ተማሪዎች ጋር በነበራቸው ቆይታ ''ከአሜሪካ እና ቻይና አንዱን እንድትመርጡ አይደለም የምንጠይቃችሁ። ነገር ግን ተገቢ ጥያቄዎችን ብቻ እንድትተይቁ ነው የማሳስባችሁ። ግልጽና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ነገሮች እየተሰሩ ነው ወይ ብላችሁ አጣሩ'' ብለው ነበር።

በአሁኑ ሰአት ምዕራባውያን አገራት ከቻይና ጋር በብድርና በመሰረት ልማት ግንባት መወዳደር እንደማይችሉ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ሁሌም ቢሆን ጉዳዩን ከሙስና፣ ዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት ጋር ያገናኙታል።

ይህን አካሄድ የተመከተ ማንኛውም ሰው የትኛውም አፍሪካዊ አገር ቻይና በኡጉር ሙስሊሞች ላይ እየፈጸመችው ነው ከሚባለው የመብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ እንደማይሳተፉ መረዳት ይችላል።