በሜክሲኮና አሜሪካ ድንበር የህፃናት ስደተኞች ቁጥር እያሻቀበ

ስደተኛ ሕጻናት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በሜክሲኮ እና አሜሪካ ድንበር አከባቢ የሚገኙ የህፃናት ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ እንደሆነ ተገለፀ።

ወደ አሜሪካ ለመዝለቅ ተስፍ ያደረጉና የሁለቱ ሀገራት ድንበር አቅራቢያ የሚገኙ ስደተኛ ህፃናት ቁጥር ከተያዘው የፈረንጆች ዓመት መግቢያ ጀምሮ በ9 እጥፍ መጨመሩን የተባበሩት መንግሥት ሕጻናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) አስታውቋል።

ሕጻናት አድን ድርጅቱ ከ380 ወደ 3ሺህ 500 ከፍ ያለው የህፃናቱ ቁጥር በሜክሲኮ የሚገኘውን የስደተኛች መቀበያ ማዕከል አጨናንቆታልም ብሏል።

የህፃናቱ መነሻ ከሆንዱረስ፣ ጓቲማላ፣ ኤልሳቫዶርና ሜክሲኮ ሲሆን ግማሽ የሚሆኑት ወላጆቻቸው አብረዋቸው እንደማይገኙ ተጠቁሟል።

የአሜሪካን ድንበር ለመሻገር ወይም ወደ መጡበት ለመመለስ በመሻት በየቀኑ ወደ 300 የሚጠጉ ህፃናት ድንበር አከባቢ እንደሚደርሱ ተመላክቷል።

በድንበሩ አቅራቢያ በምትገኘው ሬይኖሳ በተሰኘችው ከተማ ስደተኛ ቤተሰቦች ጊዜያዊ መቆያ እየገነቡ መሆኑም ተሰምቷል።

"በሜክሲኮ የሚገኙ ሕፃናት እና እናቶች የኑሮ ሁኔታ በቅርቡ የበለጠ ሊባባስ ይችላል የሚል ሥጋት አለን" ሲሉ የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን የዩኒሴፍ ዳይሬክተር ዣን ጎግ ተናግረዋል።

የህፃናቱ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በኩል ወይም ብቻቸውን ወደ ድንበር አቅራቢያ ልክው ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ የጆ ባይደን አስተዳደር ከቤተሰቦቻቸው ጋር የቀላቀሉ የሚለውን ውሳኔ እንደሚሹ በአከባቢው የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ዘግቧል።

ሆኖም የሜክሲኮ መንግሥት የስደተኞችን እንቅስቃሴ ለመግታት ወደ ሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ወተዳሮችን ማሰማሩትን የተናገረው ዘጋቢው በዚህም ምክንያት በመጪዎቹ ሳምንታት ወጣቶችን ጨምሮ ስደተኞች ሊታሰሩ ይችላሉ ቡሏል።