ከረባት አላስርም ያሉት የሕዝብ እንደራሴ ከፓርላማ ተባረሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒው ዚላንድ ማውሪ ፓርቲ መሪ የሆኑት የሕዝብ እንደራሴ ራዊሪ ዋይቲቲ ከረባት አላስርም በማለታቸው ከፓርላማ እንዲወጡ ተደርጓል።
የሕዝብ እንደራሴው ጥያቄ ለማቅረብ ሲጠይቁ አፈ ጉባኤው ትሬቨር ማልርድ ግን ከልክለዋቸዋል። በኒው ዚላንድ ፓርላማ ከረባት ያላደረገ ወንድ የሕዝብ እንደራሴ ጥያቄ እንዲያቀርብ አይፈቀድም።
የአገሪቱ መገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት፤ የሕዝብ እንደራሴው ከፓርላማ እንዲወጡ ሲደረግ "ጉዳዩ ከረባት ያለማድረግ ጉዳይ ሳይሆን ለባህል የሚሰጠው ቦታ ነው" ብለዋል።
የሕዝብ እንደራሴው ከረባትን "የቅኝ ግዛት ማነቆ" ብለውታል።
ፓርላማ ውስጥ እንዳይጠይቁ ሁለቴ ቢከለከሉም ጥያቄያቸውን ያሰሙት የሕዝብ እንደራሴው ፓርላማውን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል።
የሕዝብ እንደራሴው ራዊሪ ዋይቲቲ በማውሪዎች ዘንድ ለሥራ የሚውል ልብስ እንደለበሱና፤ ከረባት ባለማድረጋቸው ከፓርላማ እንዲወጡ መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የፓርቲው አጋር መሪ የሆነችውና ከረባት አድርጋ ፓርላማ የተገኘችው ደቢ ንጋዋፓከር የሕዝብ እንደራሴው ከፓርላማ እንዳይባረሩ ለማድረግ ብትሞክርም አልተሳካላትም።
በኒው ዚላንድ ፓርላማ ከረባትን በተመለከተ አፈ ጉባኤና የሕዝብ እንደራሴ ሲጋጩ የመጀመሪያው አይደለም።
የሕዝብ እንደራሴው ራዊሪ ዋይቲቲ ከረባት ካላደረጉ ከፓርላማ እንደሚባረሩ አምናም ተነግሯቸው ነበር።
እሳቸው ግን "ይሄን ማነቆ ከአንገቴ አውልቄ አዜማለሁ" ሲሉ መልሰዋል።
አፈ ጉባኤው ከረባትን የተመለከተው ሕግ ይቀየር ቢባል እንደሚደግፉ ተናግረው፤ አሁን ግን አብዛኞቹ የሕዝብ እንደራሴዎች ሕጉን ስለሚደግፉ ሕጉ ባለበት እንደሚጸና አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ጀሲንዳ አርደን የሕዝብ እንደራሴዎች ከረባት አናደርግም ቢሉ እንደሚደግፉ ተናግረዋል። "የኒው ዚላንድ ዜጎችን የሚያሳስባቸው ከረባት አይደለም" ሲሉም ሌሎች ጉዳዮች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።












