የአፍሪካ የጤና ኃላፊዎች ከዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ጋር ሊወያዩ ነው

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በጤና እና በፋይናንስ ዘርፍ የሚሠሩ የአፍሪካ አመራሮች ከዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ጋር ስለ ክትባት ሊወያዩ ነው።

የኮሮናቫይረስ ክትባትን ፍትሐዊ በሆነ መንግድ አህጉሪቱ ውስጥ እንዴት ማከፋፈል እንደሚቻል ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዶ/ር ቴድሮስ ከውይይቱ አስቀድመው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "አፍሪካ ውስጥ ክትባቱን ለማሰራጨት የምንችለውን ሁሉ እያደረግን እንደሆነ እነግራቸዋለሁ። ሕይወት ለማዳንና ምጣኔ ሀብቱ እንዲያገግም ለመርዳትም እንፈልጋለን። የተቀረው ዓለምም የድርሻውን መወጣት ይገባዋል" ብለዋል።

ከቀናት በፊት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎሳ፤ ሀብታም አገራት የተትረፈረፈ ክትባታቸውን ለድሀ አገራት እንዲያካፍሉ ተማጽነዋል።

የበለጸጉት አገራት ወደ 800 ሚሊዮን የሚጠጋ የክትባት ጠብታ ገዝተዋል።

የክትባት ክፍፍልን ፍትሐዊ ለማድረግ የሚሠራው ጋቪ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሴት ቤክሊ እንደሚሉት፤ ይህ ቁጥር ድሀ አገራት ክትባቱን ማግኘት ከመቻላቸው በፊት የበለጸጉ አገራትን ዜጎች ባጠቃላይ ማዳረስ የሚችል ነው።

"ሀብታም አገራት ተጨማሪ 1.4 ቢሊዮን ጠብታም አላቸው። ይህ ደግሞ የተለያዩ የክትባት አማራጮችን ያካትታል" ብለዋል።

በበይነ መረብ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፉ የምጣኔ ሀብት ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ኃላፊው፤ የበለጸጉ አገሮች ያከማቹትን ትርፍ ክትባት ለድሀ አገሮች እንዲሰጡ ለመጠየቅ እንደታሰበ ጠቁመዋል።

"እርዳታ እንዲሰጡ ጠይቀን ካልተሳካልን ክትባቱን ከሀብታም አገሮች እንገዛለን" ሲሉም እቅዳቸውን አብራርተዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር ዓለም የኮሮናቫይረስ ክትባትን እየተከፋፈለ ያለበት ሁኔታ "ለሞራል መላሸቅ የሚያጋጥ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።

ዶ/ር ቴድሮስ የክትባት ክፍፍሉ ሊፈጥር የሚችለው የሞራል ቀውስ እንደሚያሳስባቸውም ተናግረዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት ዋና የቦርድ አባላት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ዋና ኃላፊው፤ በርካታ ሀብታም አገሮች ዓለም አቀፍ የክትባት ክፍፍል ትብብር (ኮቫክስ) አሠራርን መጣሳቸውን ጠቁመዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ እንዳሉት ሀብታም አገራት የኮቫክስ የክትባት ክፍፍል ሂደትን በመጣስ ለዜጎቻቸው ክትባት እያከማቹ ነው። ይህ ደግሞ ድሀ አገራትን ችግር ውስጥ ይከታል።

ሀብታም አገራት 'ቅድሚያ ለኛ' በሚል እየሄዱበት ያለው መንገድ ድሀ አገራትና ዜጎቻቸውን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከት ዶ/ር ቴድሮስ አስምረውበታል።

ክትባት መስጠት የጀመሩ አገራት

በመላው ዓለም ከ45 በላይ አገራት ለዜጎቻቸው የኮቪድ-19 ክትባት መስጠት ጀምረዋል።

አፍሪካ ውስጥ ክትባት መስጠት የጀመሩት ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ጋና፣ ሞሪሽየስ እና ሲሸልስ ናቸው። እነዚህ አገራት ለጤና ባለሙያዎችና በከፍተኛ ሁኔታ ለቫይረሱ ለሚጋለጡ ዜጎች ክትባት እየሰጡ ይገኛሉ።

አምስቱም አገራት ክትባት ያገኙት ከበለጸጉ አገራት በድጎማ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ለፋይዘርና ባዮንቴክ ፍቃድ ቢሰጥም በአፍሪካ አገሮች እንዲከፋፈሉ ገና ይሁንታ አላሳለፈም።