የታንዛኒያ ፕሬዘዳንት ኮሮናቫይረስ "የለም" ቢሉም ቤተ ክርስቲያኗ ማስጠንቀቂያ ሰጠች

ታትሟል

የታንዛኒያው ፕሬዘዳንት ጆን ማጉፉሊ "ኮሮናቫይረስ የለም" ቢሉም የአገሪቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ስትል ማስጠንቀቂያ አወጣች።

ትላንት በተጻፈ ደብዳቤ፤ ቄስ ጊርቫስ ናይሶንጋ እንዳሉት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከናወኑ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ቁጥር ጨምሯል።

"ይህም ወረርሽኙ እንደ አዲስ እንዳገረሸ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል" ሲሉም በደብዳቤው ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ፕሬዘዳንት ማጉፉሊ "ታንዛኒያ ከኮሮናቫይረስ ነጻ ነች" ብለው እንደነበር ይታወሳል። ለአገሪቱ ጸሎት በመደረጉ ከወረርሽኙ እንደተረፈችም መሪው ተናግረው ነበር።

ማጉፉሊ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ሲቀልዱ ተደምጠዋል።

መንግሥታቸው በኮሮናቫይረስ የተያዙና ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን ቁጥር ማስታወቅ አቁሟል።

ዳሬ ሰላም ውስጥ የሚገኙት ቄስ ዩዳ ታዲ ሩዋቺ፤ ዜጎች ጤናቸውን በአግባቡ መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

"ወረርሽኙ አልቆመም። አሁንም ኮሮናቫይረስ አለ። ቸልተኛ አንሁን። ራሳችንን መጠበቅ አለብን። እጃችሁን ታጠቡ፤ ጭምብልም አድርጉ" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በአንድ ሳምንት ውስጥ ቢበዛ ሁለት የቀብር ሥነ ሥርዓት ይከናወን እንደነበርና አሁን ግን በየቀኑ ቀብር እንዳለ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጸሐፊ ቻርልስ ኪቲማ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያወጣችውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ የአገሪቱ ጤና ሚንስትር ምክትል ዶ/ር ጉድላክ ሞላል፤ ሕዝቡ ተረጋግቶ መንግሥት መግለጫ እስከሚያወጣ እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

"ጉዳዩን ለሳይንቲስቶች ብንተወው ጥሩ ነው። ችግር ካለ መንግሥት ማብራሪያ ይሰጣል። ዜጎች የእለት ከእለት ሕይወታቸውን ይግፉበት" ብለዋል ዶ/ር ጉድላክ።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሁለት ከታንዛኒያ የተነሱ ተጓዦች ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተገኘው አዲሱ የቫይረስ ዝርያ እንደተገኘባቸው ተዘግቧል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከታንዛኒያ እንዲሁም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጓዦች ላይ እገዳ የጣለችውም ባለፈው ሳምንት ነበር።

አዲሱ የኮሮናቫይረስ በተለያዩ አገሮች እየተገኘ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም የተገኙት ይጠቀሳሉ።

የታንዛኒያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጻፈችው ደብዳቤ ላይ "አገራችን ደሴት አይደለችም። ከወረርሽኙ እንድንድን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግና ወደ ፈጣሪ መጸለይም አለብን" በማለት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።