ከጎዳና ላይ ተነስቶ የጎዳና ልጆችን የሚረዳው የአዳማው ኢፋ

ኢፋ ተሊላ

የፎቶው ባለመብት, IFAA TALIILAA

ታትሟል

በልጅነቱ ወላጆቹ በመለያየታቸው ወደ ጎዳና ወጥቶ የነበረውና አሁን በሴቶች የፀጉር ሥራ ላይ የተሰማራው ኢፋ ተሊላ 105 ሕጻናትን ይደግፋል።

በተጨማሪም እርሱ በልጅነቱ ያለፈበትን የእንግልት ሕይወት ሌሎች እንዳይደግሙት በማለት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለልጆች ያደርጋል። ከሕጻናቱ በተጨማሪም ከ30 በላይ እናቶችን እንደሚደግፍም ኢፋ ይናገራል።

ኢፋ በስሙ አነስተኛ የመርጃ ማኅበር ያቋቋመ ሲሆን ለሚደግፋቸው ሰዎች የሚያስፈልጉ ድጋፎችን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያሰበስባል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ጠደቻ ቀበሌ የተወለደው ኢፋ፣ በአሁኑ ሰዓት በአዳማ ከተማ እየሰራ ባለው የሴቶች የውበት ሳሎን ራሱን ያስተዳድራል።

ኢፋ ተሊላ ማነው?

ገጠር ተወልዶ ማደጉን የሚናገረው ኢፋ ተሊላ፣ ከጨቅላ እድሜው አንስቶ በእናትና በአባት ፍቅር አለማደጉን ይገልጻል። ይህም ደግሞ ለከፋ የሕይወት ውጣ ወውረድ እንደዳረገውና አሁን በግሉ እየሰራ ላለው በጎ አድራጎት ሥራ መነሻ እንደሆነለት ይናገራል።

"በዚህች ምድር ላይ ያሳለፍኩት ችግር የእናት ጡት ወተትን ከማጣት ይጀምራል፤ እናትና አባቴ በጨቅላ እድሜዬ፣ በስድስት ወሬ፣ ተጣልተው ተለያዩ። ከዚያ በኋላ ያደግኩት በእንጀራ እናቴ እጅ ነው" በማለተት የሕይወቱን ጅማሬ ይተርካል።

በኋላ ግን ለእንጀራ እናቱም ሕይወት እየከፋ ሲሄድ ከቤት ወጥቶ፣ በግሉ የመከራ ሕይወትን መግፋት ጀመረ።

ራሴን ካወቅሁ በኋላ የገጠር ሰዎች ወደ ራሳቸው አስጠግተው ይርዱኝ እንጂ፣ ጉልበቴን ሲበዘብዙኝ ነበር የሚለው ኢፋ፣ "አራት ዓመት አካባቢ ሲሆነኝ ጉዳና ላይ ወጣሁ። እዚያም ያገኘሁትን በመብላትና ባገኘሁበት በማደር ከባድ የረሃብና የመታረዝ መከራን አሳልፌያለሁ" ይላል።

በተወለደባት ገጠር ከተማ ጎዳና ላይ ሲኖር እንደነበር የተናገረው ኢፋ፣ ሙሉ በሙሉ የጎዳና ሕይወትን የጀመረው ወለንጪቲ ከተማ ከገባ በኋላ መሆኑን ያስታውሳል።

"ገጠር ባለሁበት ሰዓት በፍፁም የማልረሳቸው ብዙ ገጠመኞች ነበሩኝ። በተለይም ዛፍ ላይ ያደርኩበትን መቼም አልረሳውም። የጅብ ድምጽ እሰማ ነበር። በጣም ያስፈራል። በጣም ይበርዳል። ከዛፉ ላይ እወድቃለሁ ብዬ ስለፈራሁ አልተኛሁም ነበር። ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ እንቅልፍ ሳይጥለኝ ነበር ያሳለፍኩት።"

ወደ ከተማ ከሄደ በኋላም በወባ በሽታ ይዞኝ በጣም በመታመሙ ሐኪም ቤት የሚወስደው ሰው ስላልነበር እሞታለሁ ብሎ ተስፋ አስከመቁረጥ መድሱን ያስታውሳል። "የሚወስደኝ ቢኖር እንኳ ልብሴና ገላዬ በጣም ከመቆሸሹ የተነሳ ወደ ሐኪም ቤት ለመሄድ ያሳፍር ነበር" የሚለው ኢፋ እድለኛ ሆኖ ከሞት ተረፈ።

ኢፋ ተሊላ

የፎቶው ባለመብት, IFAA TALIILAA

"ሲያልፍልኝ እንደኔ አይነት ሰዎችን ለመርዳት አስብ ነበር"

ራሴን ችዬ አዳማ ከተማ ከገባሁ በኋላ ትኩረቴ እንደእኔ ሕይወታቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉትን መርዳት ነው ይላል ኢፋ።

"መጀመሪያ ከአሰላ ወደ አዳማ ስንመጣ፣ 10 ልጆችን በመርዳት ነበር ይህንን ስራ የጀመርኩት። ሥራዬ እየታወቀ ሲሄድ ደግሞ መንግሥትና የተለያዩ ግለሰቦች ያበረታቱኝ ጀመር። በዚህ ሁኔታም አጠንክሬ ቀጠልኩበት።"

አስር ልጆች እንዲማሩ በመርዳት የጀመረው ኢፋ አሁኑ በአስር እጥፍ አድገው አሁን 105 ሕጻናትን እያስተማረ ይገኛል።

"ለእነዚህ ተማሪዎች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ደብተር፣ ጫማ፣ ቦርሳ፣ እርሳስ፣ እስክሪብቶ፣ ሳሙናና ቅባትን ጨምሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በሙሉ ይሰጣቸዋል" ይላል ኢፋ።

የሚማሩ ልጆችን ብቻ ሳይሆን ድጋፍ የሚፈልጉ እናቶችንም እንደሚያግዝ ኢፋ ጨምሮ ይናገራል።

"አንዲት እናት ያለማንም እርዳታ አዳማ ከተማ መንገድ ላይ በወለደች ሰዓት እኛ ነን ከጎዳና ላይ አንስተን አገልግሎት እንድታገኝ ያደረግናት። እርሷን ጨምሮ 37 የምንረዳቸው እናቶች አሉን። ለእነርሱም ዳቦ፣ ዘይት፣ ጨው፣ ስኳር፣ ቡናና አልፎ አልፎ ልብስ እንረዳለን።"

በተጨማሪ ማኅበራቸው የተቸገሩና በቤተ አምነቶች አካባቢ የሚኖሩ እንዲሁም ጎዳና ላይ ለሚገኙ ልጆች ምሳ በማዘጋጀት እንደሚመግቧቸው ይናገራል።

ኢፋ ይህንን የበጎ አድራጎት ተግባር የሚያከናውነው ብቻውን አይደለም። ገንዘቡን የሚያሰባስበው ከተለያዩ ሰዎች መሆኑን በመግለጽ፣ ሚያገኘውን የገንዘብ እርዳታ መልሶ ሌሎችን እንደሚረዳበት ይገልፋል።

"ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ልብስ አሰባስበን፣ ጎዳና ላይ ለሚኖሩት እናለብሳለን። ምግብም እንደዚሁ። በዚሁ መልክ አሁን በቅርቡ ከ60 ለሚበልጡ ጎዳና ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ተመሳሳይ እርዳታ አድርገናል።"

የማበራዊ ሚዲያ ማበሩን እንዴት አገዘው?

የማኅበራዊ ሚዲያ ለዚህ የበጎ አድራጎት ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ኢፋ ይናገራል።

"እኔ ፌስቡክ ላይ እለጥፋለሁ። ሰዎች ደግሞ እርሱን ተመልክተው ድጋፍ ያደርጉልኛል። ብዙ ሰዎች መልዕክት ይልኩልኛል። ከዚያ በኋላ የባንክ ሂሳብ ቁጥሬን ልኬላቸው በዚያ ላይ መስጠት የፈለጉትን ያህል ያስገባሉ። በአካል እርዳታ የሚያመጡ ሰዎችም አሉ" ይላል።

እየሰራን ያለነውን የተገነዘቡ ሰዎች የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች፣ ምግብ፣ ልብስ ድጋፍ ያደርጉልናል። እኛም ወዲያውኑ ድጋፉ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እናደርሳለን በማለት ሥራቸውን ያብራራል።

እየተማሩ ያሉትን ልጆች የሚደግፋቸውም፣ በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ሳይሆን፣ ከወላጆቻቸው ጋር እያሉ በመርዳት ክትትል እንደሚያደርግና እንደሚያበረታታቸው ይናገራል።

ሰውን ለመርዳት ሃብታም መሆን መስፈርት አይደለም

ሰውን ለመርዳት ሃብታም መሆን ግዴታ አይደለም የሚለው ኢፋ ለራሱ ምንም ሳይኖረው ሌሎች በርካቶች እንዲረዱ ሰበብ መሆኑን ይናገራል።

"እኔ ምንም የለኝም። የምኖረው በኪራይ ቤት ነው። በሴቶች የፀጉር ሥራ ነው ሰልጥኜ የወጣሁት። በአሁን ጊዜ ትንሽ የሴቶች የውበት ሳሎን አለኝ፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ነው ሰዎችን የምረዳው የተለየ ገቢ የለኝም"በማለት ያብራራል።

"እኔ ገንዘብ ኖሮኝ ሳይሆን ልቤ ግን ሚሊየነር ነው" በማለት ፍላጎትና መነሳሳት ካለ፣ ሃብታም ሳይኮን መደጋገፍ እንደሚቻል ይናገራል።

ማንኛውም ሰው ባለው ነገር ሰዎችን ቢረዳ ወይንም እነርሱ ባይችሉ ሌሎች እንዲችሉ ሰዎችን ቢያነሳሱ ብዙ ዜጎችን መታደግ ይቻላል ሲል ኢፋ ይናገራል።

"እኔ ኖሮኝ አይደለም ሰዎችን የምረዳው። ድጋፍ ማለት ደግሞ ገንዘብን ብቻ መስጠት አይደለም። ምክር ሞራል መስጠትና ሰዎችን ማበረታታትም ትልቅ ድጋፍ ነው" በማለት ከደካሞች ጎን መቆም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይገልፋል።

ወደፊት ምን ያስባል?

ኢፋ ወደፊት ትምህርት ቤት መክፈት እንደሚፈልግና ለዚያም እቅድ እንዳለው ይናገራል።

"የፀጉር ሥራ፣ ልብስ ስፌት፣ ሸክላ ሥራና የኮምፒውተር ስልጠናዎችን የሚሰጥበት የሞያ ትምህርት ቤት መክፈት እፈልጋለሁ" የሚለው ኢፋ፤ በዚህም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ልጆች ከእነዚህ ሙያዎች የሚፈልጉትን እንዲማሩ በማድረግ ወደፊት ሕይወታቸው እንዲያሻሽሉ ለማድረግ እቅድ እንዳለው ይናገራል።