የሌሊት ወፍ ሳንድዊች የሚበላ ሰው የሚያሳየው ማስታወቂያ ላይ ምርመራ ተጀመረ

ታትሟል

የሌሊት ወፍ ሳንድዊች ሲበላ የሚያሳይ ማስታወቂያ ላይ የአውስትራሊያው የማስታወቂያ ጥበቃ ድርጅት ምርመራ ጀመረ፡፡

ከቤት ውጭ መገልገያ አምራች የሆነው ቦቲንግ ካምፓኒ ፊሺንግ (ቢሲኤፍ) ያሠራው ይህ ማስታወቂያ በዩቲዩብ ከ 250,000 ጊዜ በላይ ታይቷል፡፡

በማስታወቂያው ለላይ ተዋናዩ ወረርሽኙ የተከሰተው አንድ ግለሰብ የሌሊት ወፍ በመብላቱ ነው ብሎ ይቀልዳል።

የመጀመሪያዎቹ የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎች በቻይና ዉሃን ከተማ ከሚገኝ የእንሰሳት ገበያ ቢገኙም፣ ቫይረሱ እንዴት እንደጀመረ እና እንደተሰራጨ ትክክለኛ ማረጋገጫ የለም፡፡

የማስታወቂያ ደረጃዎች ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የማስታወቂያ ደረጃዎች በቢሲኤፍ የበጋ ዘመቻ ማስታወቂያ ላይ በርካታ ቅሬታዎች የደረሱት ሲሆን እነዚህን ቅሬታዎች በመገምገም ላይ ይገኛል" ብለዋል።

የቢሲኤፍ ቃል አቀባይ ቀደም ሲል ለአውስትራሊያ መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት ቀለል ብሎ በቀረበው ማስታወቂያ ብዙ አውስትራሊያውያን በክረምቱ ቤታቸውን እንዲቆዩ እና የራሳቸውን ጓሮ እንዲመረምሩ ያበረታታል፡፡

"በእርግጥ የተከሰተውን ወረርሽኝ እና ስርጭት ምን ያህል እንደሆነ ተረድተናል። ይህ ግን ማስታወቂያ በተመሳሳይ መንፈስ የተቀረፀ መሆኑ ግልፅ ነው" ብለዋል።

ቢሲኤፍ ለአውስትራሊያ የማስታወቂያ ጥበቃ እንግዳ አይደለም- በጎርጎሮሳዊያኑ 2016 እና 2018 ባሠራቸው ማስታወቂያዎች ብዙ ቅሬታ ቀርቦበት ነበር፡፡

"ባለፉት ዓመታት ቢሲኤፍ ተመሳሳይ ማስታወቂያዎችን የማስነገር ባህል መሥርቷል" ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡ " ማስታወቂያዎቹ ተቺዎች ቢኖራቸውም እኛም ግን ያንን እናውቃለን" ሲሉም ያክላሉ።

የተበላሹ ግንኙነቶች

እንደባለሙያዎች ከሆነ በአውስትራሊያና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት ባለፈው ዓመት በአስርተ ዓመታት ውስጥ ከነበረበት ደረጃ ዝቅ ብሏል።

ማስታወቂያው ውጥረቱ ይበልጥ እየተለጠጠ ስለመሆኑ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

አውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ አመጣጥን ለማወቅ የሚያደረገውን ዓለም አቀፍ ምርመራን ደግፋለች፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቻይና ተማሪዎች እና ቱሪስቶች ዘረኝነትን ፍራቻ ወደ አውስትራሊያ እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው የአውስትራሊያ ምርቶች የሚገቡትም በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ትኩረት ነበር፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ቻይና በአውስትራሊያ ወይን ላይ እስከ 212% የሚደርስ ግብር ጥላለች።