ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ብሪታኒያ ከደቡብ አፍሪካ የገባ አዲስ የኮሮና ዝርያ ስጋት ውስጥ ጥሎኛል አለች
ታላቋ ብሪታኒያ አዲስ የኮሮና ዝርያ ያለባቸው 2 ሰዎችን ማግኘቷን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ማት ሐንኩክ አስታወቁ።
በሎንዶንና በሰሜን ምዕራብ ኢንግላንድ የተገኙት ሁለቱ ሰዎች ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው ከነበሩ ሰዎች ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ተረጋግጧል።
ባለፉት 15 ቀናት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው የነበሩ ዜጎች ወይም ከደቡብ አፍሪካ ከመጣ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸው በሙሉ በአስቸኳይ ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ አደራ ተብለዋል።
ይህ አዲስ ዝርያ ሰሞኑን በ70 ከመቶ ፍጥነት የመዛመት ጉልበት አለው ከተባለ ሌላ ዝርያ ጋር የሚያያዝ አይደለም።
የደቡብ አፍሪካ ጤና ሚኒስትር ዝዌሊ ምሂዜ ይህ አዲስ ዝርያ አዲስ ጭንቀት ወልዷል ብለዋል። ወጣትና በጣም ጤነኛ የሆኑ ሰዎችን ጭምር የሚያንበረክክ ዝርያ እንደሆነም አብራርተዋል።
ጤና ሚኒስትሩ ሲናገሩ "ደቡብ አፍሪካ ኤችአይቪ የመጣ ሰሞን የሆነችውን ዓይነት ምስቅልቅል ውስጥ አሁን ልትገባ አይገባትም' ሲሉ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያድርጉ ብለዋል።
ይህ ዝርያ ከተገኘ ወዲህ ሆስፒታሎች አካባቢ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ በሆነ አደገኛ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ጤነኛና ወጣት የሆኑ ሰዎች ጭምር መሆኑ ነገሩን አሳሳቢ አድርጎታል።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ይህ አዲሱ የኮቪድ ዝርያ በጣም በፍጥነት እንደሚዛመት ደርሰንበታል እያሉ ነው።
አዲሱ ዝርያ አሁንም ገና ምርምር እየተደረገበት ቢሆንም ከእስከዛሬዎቹ የዝርያ አይነቶች ሁሉ በአስደንጋጭ ፍጥነት እየተዛመተ ስለመሆኑ ግን አጠራጣሪ አልሆነም።
ይህ አዲስ ከደቡብ አፍሪካ መጣ የተባለ ዝርያ ታላቋ ብሪታኒያ በዚህ ሳምንት መጀመርያ አጋጠመኝ ካለችው ሌላ አዲስ ዝርያ ጋር ተመሳሳይነት አለው።
ሁለቱም ዝርያዎች N501Y የተሰኘ ቅንጣት ያላቸው ሲሆን የሰዎች ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ከፍተኛ ማጥቃት የሚሰነዝረው ይህ ራሱን የሚያባዛ ቅንጣት ነው።
በኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ሎንዶን ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ፈርጉሰን "ሊያሳስበን የሚገባው ከደቡብ አፍሪካ መጣ የተባለው ነው" ይላሉ።
ምክንያቱን ሲያስረዱም ይህ የተህዋሲ ዝርያ በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎችን የሚያዳርስበት መንገድ የፍንዳታ ያህል ነው ሲሉ ነው የገለጹት።
ታላቋ ብሪታኒያ ነገሩ ጭንቅ ሆኖባታል። በርካታ የአውሮጳ አገራትም አዲሱን ዝርያ በመፍራት በሳምንቱ መጀመርያ አካባቢ የአየርና የየብስ ግንኙነቶችን መዝጋት ጀምረው ነበር።
ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ በርከት ያሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ጥላለች።
ደቡብ አፍሪካ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝቧ በተህዋሲው የተነካ ሲሆን 25ሺ ዜጎች ሞተዋል፥ ይህም በአፍሪካ ትልቁ አሐዝ ሆኖ ተመዝግቧል።