በኳታር አየር ማረፊያ መጸዳጃ ቤት ተጥላ የተገኘችው ሕጻን እናት ማንነት ታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኳታር የወላጆቿ ማንነት ለሳምንታት ሳይታወቅ የቀረውን ተጥላ የተገኘች ልጅ እንቆቅልሽ መፍታቷን አስታወቀች።
የዚህች ጨቅላ ልጅ ወላጅ እናት ኢሲያዊት ናት ብለዋል የኳታር ባለሥልጣናት። ሕጻኗ የተገኘችው በአየር መንገዱ መጸዳጃ ቤት ውስጥ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ ተጥላ ነበር።
በዶሃ አየር መንገድ ሽንት ቤት ውስጥ ተጥላ የተገኘው ሕጻን የወላጆቿን ማንነት ለማግኘት የኳታር ፖሊስ ባደረገው መጠነ ሰፊ ምርመራ አገሪቱ ከአውስትራሊያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ አተካራ ውስጥ መግባቷ ይታወሳል።
ይኸውም የሕጻኗን መጸዳጃ ቤት ተጥላ መገኘት ተከትሎ የአውስትራሊያ ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ሴቶች የልጅቷ እናት ስለመሆናቸው 'አጸያፊ' የተባለ ፍተሻ በአየር ማረፊያ ፖሊሶች መካሄዱን ተከትሎ ነው።
ከአውስትራሊያዊን ሴት ተጓዦች ባሻገርም የታላቋ ብሪታኒያና የኒውዚላንድ ሴት ተጓዦች በተመሳሳይ በምርመራ ሂደት ለእንግልት ተዳርገናል ብለው ቅሬታ አቅርበው ነበር።
ሴቶች በቅርቡ ልጅ ስለመውለዳቸው የሚያሳይ መልክት ካላቸው በሚል ነበር ፍተሻው የተካሄደባቸው።
አሁን የኳታር ዐቃቢ ሕግ እንዳለው ከሆነ ሕጻኗን ልጅ መጸዳጃ ቤት ጥላ የኮበለለችው አንዲት የኢሲያ አገር ዜግነት ያላት ሴት መሆኗን ደርሼበታለው ብሏል።
የዲኤንኤ ምርመራው እንዳረጋገጠው በፌስታል ተጠቅልላ የተጣለችው ልጅ አባትም ኢሲያዊ ዝርያ ያለው ሰው ነው።
ዐቃቢ ሕግ ጨምሮ እንዳብራራው የልጅቷን በመጸዳጃ ቤት ተጥላ መገኘትን ተከትሎ በሴት ተጓዦች ላይ አላስፈላጊ ምርመራ ያደረጉ የኢሚግሬሽን ኃላፊዎችም ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ነገሩ ያልተመለደ በመሆኑ በዚያ ዕለት በረራ ያደርጉ በነበሩ 10 አውሮፕላኖች ውስጥ ተጓዥ የነበሩ ሴቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ምርመራዎች ተደርገዋል።
በተለይም ወደ ሲድኒ መዳረሻቸውን ያደረጉና ኳታር አየር መንገድን ተሳፍረው የነበሩ ሴቶች ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ተደርገው በአምቡላንስ ተወስደው፣ ልብሳቸውን አውልቀው የግዳጅ ምርመራ እንዲያደርጉ መደረጋቸው ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ድርጊቱ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ብለውታል።
የኳታሩ አቻቸው ሼክ ካሊድ ቢን ካሊፋ አል ታኒ በበኩላቸው በአስትራሊያ ዜግነት ባላቸው ሴቶች ላይ የተፈጸመው እንግልት ተገቢ እንዳልነበረ ሲሉ ጠቅሰው በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ሴት ተሳፋሪዎችን ለግዳጅ ምርመራ የዳረጉት የአውሮፕላን ጣቢያው መርማሪዎች ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን እስከ ሦስት ዓመት ሊታሰሩ ይችላሉ ተብሏል።
ዐቃቢ ሕግ ትንሽዋን ልጅ መጸዳጃ ቤት የጣለቻት ሴት ተላልፋ እንድትሰጠው ጠይቋል። እስከ 15 ዓመት እስር ይጠብቃታልም ተብሏል።
የኳታር መንግሥት የተጣለችው ልጅ እናት የኢሲያዊት አገር ዜጋ ናት ከማለት ውጭ የአገሪቱን ስም ይፋ አላደረገም።
በተጣለችው ልጅ አባት ላይ እስካሁን ክስ አልተመሰረተም።
ተጥላ የተገኘችው ልጅ አሁን በኳታር ባለሥልጣናት እንክብካቤ እየተደረገላት ነው።












